ኢሳት ዜና (ታህሳስ 18 ፣ 2008)
ከአንድ ወር በላይ የዘለቀውና፣ ለአንድ ሳምንት ጋብ ብሎ የሰነበተው ተቃውሞ፣ ካለፈው ዓርብ ጀምሮ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ዳግም መቀስቀሱ ተገለጸ።
በመላው ኦሮሚያ ክልል የተነሳው ተቃውሞ፣ ለተወሰነ ጊዜ ጋብ ያለ ቢመስልም፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በምዕራብና ሰሜን ሸዋ በተለያዩ ከተሞች ዩንቨርስቲዎችና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተቀጣጥሎ መቀጠሉ ታውቋል። ባለፈው ዓርብ ማለትም በወለጋ ዩንቨርስቲ፣ በሰሜን ሸዋ ወረዳዎች፣ ቱሉ ሚልኪ እንዲሁም በአሰበ ተፈሪ (ጭሮ) ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ህዝቡና ተማሪዎች አደባባይ በመውጣት ቁጣውን የገለጹ ሲሆን፣ ተማሪዎቹ የታሰሩ ጓደኞቻቸው ካልተፈቱ ወደ ትምህርት ገበታ እንደማይመለሱ አስታውቀዋል። የአምቦ ዩንቨርስቲ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በሄሊኮፕተር የተጋዙ የመንግስት ሃይሎች ከበባ ፈጽመው የተማሪዎች ማደሪያዎች ሰብሮ በመግባት መደብደብና ማሰራቸው የታወቀ ሲሆን ተማሪዎች የአጋዚ ጦር ግቢውን ለቆ ካልወጣ ትምህርት አንቀጥልም ብለው ወደ የቤታቸው መሄዳቸው ተገልጿል።
ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተፈጸመበት በአምቦ ዩንቨርስቲ አሁንም ወታደራዊ ካምፕ በሚመስል መልኩ በሰራዊት መጥለቅለቁን ለማወቅ ተችሏል።
መንግስት ተማሪዎች ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት ስብሰባ እንዲሳተፉ ያደረገው ጥሪና ግፊት ውጤት አለማምጣቱን ለማወቅ ተችሏል። በአንቦ ዩንቨርስቲ በፖሊስ ዱላ የተጎዱ ተማሪዎች ወደ ሆስፒታል ተወስደው እርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ ወደእስር ቤት እንደተወሰዱ ታውቋል። አብዛኛው ተማሪም ግቢውን ለቆ ወጥቷል ተብሏል።
የአምቦ ተማሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት፣ አሁን ባለው ሁኔታ መንግስትና ህዝብ ሆድና ጀርባ ሆነዋል ብለዋል። በወለጋ ሆሮ ጉድሩ፣ በሰሜን ሸዋ ኤጂሬ እና ሂጁቡ አቦ ተማሪዎች ከመንግስት ሃይሎች ጋር መጋጨታቸው የተገለጸ ሲሆን አንድ ተማሪ በስለት መወጋቱና ሆስፒታል መወሰዱን ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ስር ዝርዝር አካትቶ ባወጣው ረፖርት እስካሁን 122 ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል።