በማላዊ 34 ኢትዮጵያውያን ለእስር ተዳረጉ

ኢሳት (ግንቦት 1 2008)

የማላዊ መንግስት ወደ ሃገሪቱ በህገ-ወጥ መንገድ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ መጨመሩ አሳስቦት እንደሚገኝ ሰኞ አስታወቀ።

በቅርቡ 16 ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር እንዳዋሉ የገለለጹት የሃገሪቱ የጸጥታ ሃይሎች በሳምንቱ መገባደጃ እሁድ 34 ኢትዮጵያውያን በህገወጥ መንገድ ወደ ማላዊ ገብታችኋል ተብለው ለእስር መዳረጋቸው ገልጸዋል።

በፀጥታ ሃይሎች ከተያዙት ስደተኞች ኢትዮጵያውያኑ መካከል እንደኛው ክፉኛ ድብደባ ተፈጽሞበት ካቶንድዌ በሚባል ግዛት የህክምና እርዳታ እየተደረገለት እንደሚገኝ ሉሳካ ታይምስ የተሰኘ ጋዜጣ ፖሊስን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

የሉአንግዋ ግዛት ፖሊስ ኮሚሽንነር የሆኑት ማታኣ ሙለታ 34 የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን የዛምቢያ ወንዝን በማቋረጥ ወደ ዚምባብዌ ለመግባት ሙከራን በሚያደርጉ ጊዜ በነዋሪዎች ጥቆማ በእስር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

በየጊዜው ወደ ሃገሪቱ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጨመረ መምጣቱን ያስታወቁት የፖሊስ ሃላፊው ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ መዳረሻቸው ደቡብ አፍሪካ እንደነበር አክለው አስታውቀዋል።

በቡድን እየተደራጁ ወደ ዛምቢያ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ኣየጨመረ መምጣቱን ተከትሎም የሃገሪቱ ፖሊስ ህብረተሰቡ ጥቆማን በመስጠት ኣንዲተባበር ጥያቄ ማቅረቡን ጋዜጣው በዘገባው አስፍሯል።

በቅርቡ በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ ሃገሪቱ ገብተዋል ተብለው ለእስር የተዳረጉ 16 ኢትዮጵያውያንም ክስ ተመስርቶባቸው ዉሳኔን እየተጠባበቁ ሲሆን 34ቱ ኢትዮጵያውያንም በተያዘው ሳምንት ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በነዋሪዎች ክፉኛ ተደብድቦ ሆስፒታል የሚገኘው አንድ ኢትዮጵያዊም ከሆስፒታል ከወጣ በኋላ ፍርድ ቤት ቀርቦ ተመሳሳይ ክስ እንደሚጠብቀው የዛምቢያ ፖሊስ አክሎ ገልጿል።

በተያዘው ወር ብቻ ወደማላዊ በህገ-ወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለው ለእስር የተዳረጉ ከ20 የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን እስከ ስድስተኛው ወር በሚደርስ የእስር ቅጣት እንደተላለፈባቸውም ለመረዳት ተችሏል።

ከዛምቢያ በተጨማሪ በጎረቤት ማላዊ፣ ታንዛኒያ እና ሌሎች ጎረቤት ሃገራት በመቶች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በእስር ቤቶች እንደሚገኙም የየሃገሪቱ ፖሊሶች በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ያለውን አለመረጋጋት በመሸሽ ከሃገሪቱ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ መጨመሩን የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት (IOM) እና ሌሎች አካላት በመግለጽ ላይ ሲሆኑ በተለይ ጦርነት እልባት ወደ አላገኘባት የመን የሚደረገው የኢትዮጵያውያን ስደት እጅግ አሳሳቢ መሆኑን እነዚሁ አካላት አስታውቀዋል።