በማላዊ የእስር ቅጣት ያጠናቀቁ 165 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በእንግልት ላይ መሆናቸውን ተነገረ

ኢሳት (ሃምሌ 19 ፥ 2008)

በህገወጥ መንገድ ወደ ማላዊ ገብታችኋል ተብለው የተላለፈባቸውን የእስር ቅጣት ያጠናቀቁ 165 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሃገሪቱ በእንግልት ላይ መሆናቸውን የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) ማክሰኞ ገለጠ።

በሃገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ስደተኞችን ሁኔታ ለመመልከት በቅርቡ የባለሙያ ቡድንን ወደ ማላዊ ልኮ እንደነበር ያስታወቀው ድርጅቱ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለው ለእስር የተዳረጉ 165 ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን አስታውቋል።

የማላዊ መንግስት ስደተኞቹ ላይ ከሶስት እስከ ዘጠኝ ወር የሚደርስ የእስር ቅጣት ቢያስተላልፍም ስደተኞቹ የእስር ቅጣታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ሃገራቸው የሚመልሳቸው አካል በመጥፋቱ ለስቃይ ተዳርገው እንደሚገኙ ታውቋል።

እነዚሁ ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ይረዳ ዘንድ የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

በማላዊ የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ግለሰቦች የእስር ቅጣታቸውን የጨረሱት ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ መብት ጥሰት እየደረሰባቸው ነው በማለት ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ባለፈው ወር ዘመቻ መክፈታቸው ይታወሳል።

የማላዊ መንግስት በበኩሉ ስደተኞቹን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በጀት የሌለ በመሆኑ ኢትዮጵያውያኑ በእስር ቤት መቆየታቸውን ገልጿል።

በሶስት እስር ቤቶች በተጨናነቀ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ የተባሉት 165ቱ ኢትዮጵያውያን ሰደተኞች በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ዳቦ እየቀረበላቸው እንደሚገኝ የማላዊ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን ኢትዮጵውያን በቅርቡ ወደ ሃገራቸው ለማጓጓዝ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጦርነት እልባት ባላገኘባት የመን መውጫን አጥተው የነበሩ 150 ስደተኞች ኢትዮጵያውና ከቀናት በፊት ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን ድርጅቱ አክሎ አስታውቋል።

ባለፈው የፈረንጆች አመት 2015 ብቻ ከ70ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ የመን መሰደዳቸው ይታወሳል።