ኢሳት (ግንቦት 26 ፥ 2008)
በማላዊ እስር ቤት ለእስር ተዳርገው የሚገኙ ከ100 በላይ ስደተኞች ኢትዮጵያውያን በምግብ አቅርቦት ችግር እየተሰቃዩ መሆኑን የማላዊ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
ስደተኞቹ ያሉበትን አስከፊ ሁኔታ በመቃወም የሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ከቀናት በፊት ጉዳዩ እልባትን እንዲያገኝ ዘመቻ መክፈታቸው ይታወሳል።
በስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ ሁኔታ ተቃውሞአቸውን እየገለጹ ያሉት አካላት ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ አልያም ወደሌላ እስር ቤት እንዲዛወሩ እንዲደረግ በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን ኒያሳ ታይምስ የተሰኘ የማላዊ ጋዜጣ በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ሪፖርት አመልክቷል።
አብዛኞቹ ስደተኞች ያለምንም የምግብ አቅርቦት ለቀናት የሚቆዩበት ጊዜ መኖሩን ያስነበበው ጋዜጣው በተለይ ህጻናት ስደተኞቹ ከፍተና ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ዘግቧል።
ሉሎንግዌ ተብሎ በሚጠራው ግዛት በሚገኘው የካቺሬ እስር ቤት በርካታ ህጻናት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን፣ የህጻናቱ ሁኒታ እጅግ አሳሳቢ ነው ሲሉ የማላዊ የሰብዓዊ መብትና የህግ አገልግሎት ማዕከል ተጠሪ የሆኡንት ዊሊያም ምሃንጎ ለመገናኛ ብዙሃን አስታውሰዋል።
ስደተኞቹ ካሉበት ዘርፈ ብዙ ችግር በተጨማሪ በእስር ላይ የሚገኙበት ህንጻ ከማርጀቱ የተነሳ በማንኛውም ሰዓት ሊፈርስባቸው እንደሚችልም ሃላፊው ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሁኔታን በመረዳት ዘመቻው መግፋቱን ያወሱት ዊሊያምስ የስደተኞቹ ቁጥር 120 ነው ቢባል ትክክለኝ ቁጥሩን ለማወቅ በአግባብሩ እንዳለቻለም ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።
ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ደድዛ ሞኡላ እና ምዙዙ ተበለው በሚጠሩ እስር ቤቶች የሚገኙ ሲሆን፣ በእስር ቤቶች ካለው መጨናነቅ የተነሳ ተላላፊ በሽታዎች ሊቀሰቀሱ ይችላል ተብሎ ስጋት መኖሩንም ለማላዊ መገናና ብዙሃን ዘበዋል።
የማላዊ ፍ/ቤት ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ገበተዋል ብሎ እስከ ዘጠኝ ወር የሚደርስ ቅጣት ቢያስተላልፍባቸውም የቅጣት ጊዜያቸውን ጨርሰው እስከ ሁለት አመት ድረስ በእስር ቤቱ የቆዩ መኖራቸው ታውቋል።
የማላዊ የኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት በበኩሉ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በጀት አለመኖሩ የገልጹ ሲሆን ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል እስካሁን ድረስ የተሰጠ ምላሽ የለም።