በማላዊ ታስረው ከሚገኙት ኢትዮጵያውያን 14 ህጻናትን መታደጉን አለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት አስታወቀ

ኢሳት (ሰኔ 3 ፥ 2008)

የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት በማላዊ እስር ቤቶች ለከፋ የምግብ እጥረት ከተዳረጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መካከል 14 ህጻናት መታደግ መቻሉን አስታወቀ።

የማላዊ መንግስት በበኩሉ ወደሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለው የተላለፈባቸውን የእስር ቅጣት ያጠናቀቀ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በገንዘብ እጥረት የተነሳ ወደሃገራቸው ሊመለሱ አለመቻሉን ገልጿል።

የሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በበኩላቸው በሶስት እስር ቤቶች የሚገኙ ከ100 በላይ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ለከፋ የምግብ እጥረት በመጋለጣቸው ምክንያት ስደተኞቹ ከእስር ቤቶቹ እንዲወጡ አልያም ወደሃገራቸው እንዲመለሱ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ዘመቻን ከፍተዋል።

ለዚሁ የማላዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ምላሽን የሰጠው የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት እድሚያቸው ከ 12 እስከ 17 አመት የሆናቸው 14 ህጻናትን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ማድረጉን አርብ አስታውቋል።

ይሁንና ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ የገንዘብ እጥረት መኖሩን ያስታወቀው ድርጅቱ ሌሎች አካላት ኢትዮጵያውያኑን ለመታደግ ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

ባለፉት አምስት ወራቶች ብቻ ድርጅቱ በአስር ሃገራት ተመሳስይ ችግር ውስጥ የነበሩ 1,657 ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሃገር ሊመልስ መቻሉን አክሎ ገልጿል።

የማላዊ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ወደ ሃገሪቱ ገብተዋል ያላቸውን በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር አውሎ የሚገኝ ሲሆን፣ ከበጀት እጥረት ጋር በተገናኘ ስደተኞቹ ምግብ ሳይቀርብላቸው የሚያሳልፉበት ቀን መኖሩን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የማላዊ መንግስት ስደተኞቹን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በጀት የሌለ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን የተላለፈባቸውን ቅጣት ከጨረሱ በኋላ እስከ ሁለት አመት ድረስ በእስር ቤት የሚቆዩበት ሁኔታ መኖሩን አስታውቀዋል።

የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅትና የተባበሩት መንግስታት ህጻናት መርጃ ድርጅት ስደተኞቹን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ጥረትን በማድረግ ላይ ቢሆኑም፣ የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ የሰጠው ምላሽ የለም።