ሐምሌ ፳ ( ሀያ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቦረና ዞን በሚኦ ወረዳ ሂዲ ሎላ ከተማ በተነሳው ህዝባዊ አመጽ አንድ ሰው ሲገደል ሁለት ሰዎች ደግሞ ክፉኛ ቆስለዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች “ሞያሌ ከተማ በሁለት ክልሎች መተዳደሩ ተገቢ ባለመሆኑ ወደ ኦሮምያ ክልል ይጠቃለል፣ ዩኒቨርስቲ ይከፈትልን፣ ፍትህ ይሰጠን፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶቻችን ይከበሩልን፣ የወያኔን የመከፋፈል ፖሊሲ እንቃወማለን፣ ይህ መንግስት አይወክለንም፣ አያስተዳድረንም “ የሚሉ እና ሌሎችንም አካባቢዊ ጥያቄዎች አንስተዋል። የአሁኑ ሰልፍ ባለፈው ሳምንት በያቤሎ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ የተዘጋጀ ነው። በያቤሎ ተካሄዶ በነበረው ሰልፍ የወረዳው ባለስልጣናት በአገር ሽማግሌዎች በኩል በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ መልስ እንደሚሰጡ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን መልስ አልሰጡም። በዛሬው አመጽ ቃባር ቀርባቶ የተባለ ሰው ሲገደል፣ ሌሎች ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል። ትናንት 6 ሰዎች ተይዘው መታሰራቸውን የአካባቢው ሰዎች ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በምስራቅ ሸዋ ዞን ከሞጆ ከተማ 5 ኪ/ሜ ርቀት ላይ በምትገኘዋ ኤጀርሳ ከተማ ህዝቡ በድንጋይ መንገድ በመዝጋት ተቃውሞ በማስነሳቱ ወደ ሻሸሜ የሚደረግ ጉዞ ተቋርጦ መዋሉ ታውቋል። በኦሮምያ እንደገና የተጀመረውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመቆጣጠር ገዢው ፓርቲ የአጋዚ ሰራዊት አባላትን በስፋት እያሰማራ ነው። የፌደራል ፖሊስ አባላት አገሪቱን በሃይል መቆጣጠር እንደማይቻልና ፖለቲካ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ እየወተወቱ ቢሆንም፣ ገዢው ፓርቲ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን የፌደራል ፖሊስ ልብስ በማልበስ ተቃውሞዎችን በሃይል ለመጨፍለቅ መወሰኑን ምንጮች ይገልጻሉ።