ኢሳት (ሚያዚያ 10 ፥ 2008)
ነዋሪነታቸው በዚህ በአሜሪካ ሚኒያፖሊስ ግዛት ሚኒሶታ ከተማና አካባቢዋ የሆኑ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ግንቦት ሰባትን ለመደገፍ በሳምንቱ መገባደጃ እሁድ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት አካሄዱ።
የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች የተለያዩ ሃይማኖት ተወካዮች በተገኙበት በዚሁ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ከ64ሺህ ዶላር በላይ መገኘቱንም ፓርቲው ለኢሳት በላከው መግለጫ አመልክቷል።
በዚሁ የሚኒሶታው ዝግጅት በቅርቡ የአርበኞች ግንቦት ሰባት የተቀላቀለችው ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ፣ የኢትዮጵያ አየር ሃይል አባል የነበሩት ካፒቴን ተሾመ ተንኮሉ ፣ የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ታጋይ አቶ ሚካዔል እምሩ እንዲሁም ሌሎች ታዋቂ እንግዶች ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል።
በዝግጅቱ ወቅት ወቅታዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካና የማህበራዊ ጉዳዮች ሰፊ ውይይት ተካሄዶባቸው እንደነበርና የገቢ ማሰባሰቢያው በስኬት መከናወኑን የፓርቲው የሚኒሶታ ግብረ-ሃይል ገልጿል።