የካቲት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፍትሕ ራዲዮ እንደዘገበው፤በአዲስ አበባ ብቻ ከ800 -1000 የሚደርሱ ሰዎችን ለማሰር ታቅዷል፡፡
የሙስሊሙን ማህበረሰብ አካላት በምክንያት ለማሰር በከፍተኛ የኢትዬጲያ መንግስት የደህንነት ሃይሎች የሚመራ ዘመቻ መከፈቱን ፍትህ ራዲዬ ዘግቧል።
ራዲዮው ምንጮቹን በመጥቀስ እንደዘገበው፤ዘመቻው ያነጣጠረው፤ ከመጪው ሃገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ በህዝበ-ሙስሊሙ መካከል ትልቅ ንቅናቄ ይፈጥሩ ይሆናል የሚል ስጋት ባሳደሩ ሙስሊሞች ላይ ነው።
መንግስት ምርጫው ከመድረሱ አስቀድሞ በሃገሪቱ እየተንቀሳቀሱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተለያዩ ምክንያቶች ሲያዳክምና ሲያግድ ከመቆየቱም በላይ የግል ፕሬስ ጋዜጠኞችን ለእስርና ለስደት መዳረጉ ይታወቃል።
በአሁኑ ወቅት ሳይታገዱ የቀሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለኢህአዴግ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉት በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ ብቻ መንጠላጠል ከቻሉ ነው የሚል ግምገማ የወሰደው ኢህአዴግ፤ በዚህም መሰረት በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ የመጨረሻ የማዳከም ዘመቻ መከፈት አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱ ተመልክቷል።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የኦሮሚያ ክልሎች የአሰሳ እና ስምሪት ተግባር እየተካሄደ ሲሆን፤በተለይ በአዲስ አበባና በጅማ በርካታ ሙስሊሞችን በጅምላ የማሰሩ ዘመቻ ተጀምሯል።
እንደ ምንጮቹ መረጃ፤በከፍተኛ የደህንነት ሀይሎች በሚመራው በዚህ ዘመቻ፤ ሃገር አቀፍ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት በአዲስ አበባ ብቻ ቁጥራቸው ከ 800 እስከ 1000 የሚደርሱ ሰዎችን ለማሰር እቅድ ተይዟል።
በዛሬው ዕለትም የራዲዬ ቢላል ጋዜጠኛ የነበረው ካሊድ መሐመድን ጨምሮ ቁጥራቸው እስካሁን በውል ያልታወቀ በርካታ ሙስሊሞች ከያሉበት በደህንነት ሃይሎች እየታፈኑ ወደ እስር ቤት እየተወሰዱ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡
ሙስሊሞቹ በተያዙበት አካባቢዎች በወደሚገኙ የፖሊሰ ጣብያዎች እየታጎሩ ሲሆን፤ የመኖሪያ ቤታቸውም በፖሊሶች እና በደህንነቶች እየተፈተሸ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ቤታቸው የሚገኙ የተለያዩ ላፕቶፕ እና የግል ንብረቶቻቸውም “ለምርመራ ያስፈልጋሉ” እየተባሉ በደህንነቶች መወሰዳቸው ታውቋል፡፡