በሙስሊሞች ላይ መንግስት ጠጣር የሀይል እርምጃ ይወስዳል የሚል ስጋት እንዳለ ተነገረ

ግንቦት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-መቀመጫውን በለንደን  ያደረገው ዓለማቀፉ “ኮንትሮል ሪስክ” ድርጅት ፤የ ኢትዮጵያ ሙስሊሞች በተቃውሟቸው እየጠነከሩ ከመጡ መንግስት ጠጣር የሀይል እርምጃ ይወስዳል የሚል ስጋት እንዳለው ገለጸ።

የድርጅቱ የውዝግቦች ጉዳይ ተንታኝ ሚስተር ፓትሪክ ሜየርን ከዶቸ ቨለ የ አማርኛው ክፍል ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ባደረጉት ቃለ-ምልልስ፤ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ቀንድ አክራሪ እስልምናን በመቋቋም ረገድ፣ የምዕራቡ ዓለም ተጓዳኝ መሆኗን እና ይህን በማከናወን ረገድ በተለይ በሶማልያ መሪ ሚና እንዳላት አውስተዋል።

 በዚያም በተለይ በደቡብና በማዕከላዊው ሶማልያ እስላማዊ አክራሪነትን ለመታገል ኢትዮጵያ በወታደራዊ ኃይል ጣልቃ እስከመግባት መድረሷን ያወሱት ፓትሪክ ሜየርን፤በቅርቡም ኬንያንና የ አፍሪቃ ህብረትን ከመሳሰሉ አገሮች ጋር በመሰለፍ አልሸባብን ለመውጋት መሰማራቷን ጠቅሰዋል።

ሬዲዮው ፤ለሚስተር ፓትሪክ ሜየርን ካቀረበላቸው ጥያቄዎች መካከል፦“በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የለም፤ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደቀጠለ ነው፤ የፕሬስ ነጻነት ከባድ ፈተና ላይ ወድቋል እያሉ የሚጽፉና የሚያሰሙ፤ መገናኛ ብዙኀን አሉ። በእንዲህ ሁኔታ፤ እንዴት ነው የምዕራቡ ተጓዳኝ ሆና የምትቀጥለው?” የሚለው አንዱ ነበር።

ሚስተር ሜየርን ለዚህ በሰጡት ምላሽ፦”ከምዕራባውያን መንግሥታትና ተቋማት፣ ኢትዮጵያ የውስጣዊ አስተዳደሯን ጉዳይ እንድታስተካክል ግፊት ቢኖርም፣ ተጨባጩ ሁኔታ እንደሚያሳየን፤ በተለይ ዩናይትድ ስቴትስን የመሳሰሉ አገሮች በአፍሪቃው ቀንድ የአሸባሪነት ሥጋትን በተመለከተ ነው ቅድሚያ  ትኩረት የሚያደርጉት”ብለዋል።

ድርጅታቸው የ ኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ በሰነዘሩ እና ተቃውሞ ባሰሙ ሙስሊሞች ላይ እርምጃ ይወስዳል ሲል ምን እንደሆነ  ያብራሩ ዘንድ ለቀረበላቸው  ተከታይ ጥያቄ ግን፤”በነዚህ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ አስተያዬት ከመስጠት እቆጠባለሁ” ነው ያሉት-የኮንትሮል ሪስክ የውዝግቦች ጉዳይ ተንታኙ ሚስተር ፓትሪክ ሜየርን።

ሚስተር ፓትሪክ ፤የኢትዮጵያ መንግስት ተቃውሞው እየጠነከረበት ከመጣ፤ ጥያቄ በሚያነሱት  ሙስሊሞች ላይ የሀይል እርምጃ እንደሚወስድ ድርጅታቸው ስለደረሰበት ትንተና ያብራሩ ዘንድ ሲጠየቁ ፦’በዚህ ጉዳይ ላይ ብቆጠብ እመርጣለሁ” ቢሉም፤ ወደዚያ ድምዳሜ የደረሱት ከኢትዮጵያ መንግስት ያለፈ ልምድ እና ባህሪ በመነሳት እንደሚሆን ብዙዎች ያምናሉ።

በአርሲ-አሰሳ፦” ድምፃችን ይሰማ!ህገ-መንግስታዊ መብታችን ይከበር!” ብለው በጠየቁ ሙስሊሞች ላይ የፌዴራል ፖሊሶች  በወሰዱት የሀይል እርምጃ 7 መገደላቸውና በርካቶች መቁሰላቸው አይዘነጋም።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide