ጥር 24 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በሙስሊም ምእመናን ከፍተኛ ተቃውሞ እየደረሰበት ያለውን “የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት” (መጅሊስ) ለመታደግ፤ ኢህአዴግ “በሽምግልና” ስም ጣልቃ መግባቱ ተሰማ።
በኢህአዴግ ሸምጋይነት በዛሬው ዕለት በመጅሊሱ መሪዎች እና ብዙሀኑን ምእመን በሚወክሉት ጊዜያዊ ወኪሎች መካከል ሊደረግ የነበረው ውይይት፤ ሳይካሄድ ቀርቷል።
በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ በሽፈራው ወልደማርያም እና በሚኒስትር ጁነዲን ሳዶ አወያይነት ይካሄዳል ተብሎ የነበረው ይህ ሽምግልና ሳይጀመር የቀረው በምን ምክንያት እንደሆነ እስካሁን በተብራራ ሁኔታ ባይታወቅም፤ በመጅሊሱ እና በአዲሱ የተወካዮች ቡድን መካከል እውቅና የመስጠት ጉዳይ ሳይነሳ እንዳልቀረ ምንጩን በመጥቀስ አዲስ ነገር ዘግቧል።
በአወሊያ ትምህርት ቤት በተነሣውና በመጅሊሱ ጣልቃ ገብነት ሳቢያ ተፈጠረ በተባለው አለመግባባት የተለኮሰው የተማሪዎች ተቃውሞ እየሰፋ ሄዶ ብዙኀኑ ሙስሊሞች መጅሊሱ እንደ አዲስ እንዲዋቀር ያላቸውን ጥያቄ እያሰሙ እንደሚገኙ ይታወቃል።
ከአራት ሳምንታት በላይ ባስቆጠረው በዚህ የጁምአ ድህረ-ጸሎት ተቃውሞ ፤ የምእመናኑ ጥያቄና ቁጣ እየጠነከረ መምጣቱ፤ “ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ሊያነሣሳብኝ ይችላል በሚል ስጋት” ኢህአዴግ መራሹን መንግስት ክፉኛ እንዳስጨነቀው የፖሊስ ምንጮቻችን ጠቁመዋል።
የምእመናኑ ዋነኛ ጥያቄም ፦”መጅሊሱ በአመራሩ የመንግሥት የፖለቲካ መጠቀሚያ ሆኗል፣ የምእመናንን ፍላጎትና ጥያቄ መወከል አይችልም፣ አመራሮቹም በሕዝብ የተመረጡ ሳይሆኑ በፖለቲካ ጫና የተቀመጡ ናቸው። ምእመናን መሪዎቻቸውን የመምረጥ መብታቸው ይከበር!እና የመጅሊሱ አመራር በ አስቸኳይ ይቀየር!” የሚል ነው።
ለጊዜው ጉዳዩን ችላ ያሉ ለመምሰል የሞከሩት መጅሊሱ እና መንግሥት ጥያቄውን “የአክራሪዎች ነው” በማለት ለማጣጣል ሲሞክሩ የቆዩ ሲሆን፤ ህዝባዊ ቁጣው እየጋመና እየተቀጣጠለ ሲመጣ አጣብቂኝ ውስጥ በመግባታቸው ፤በሽምግልና ስም ሁለቱን ወገኖች ለማነጋገር እንደወሰኑ ለመረዳት ተችሏል።
ሆኖም፣ ኢህአዴግ በሽምግልና ስም ጣልቃ ሲገባ፤ ጉዳዩን የአብዛኛውን ሙስሊም መሠረታዊ የመብትና የሕግ ጥያቄዎቹን በሚመልስ መልኩ ለማስተናገድ ወስኖ ይሆን? ወይም እንደተለመደው ነገሩን የማድበስበሻ ስልት ፍለጋ የሚለው አልታወቀም።
መንግሥት ከወራት በፊት “አሐበሽ” የተባለውን አስተምህሮ ከተቀሩት የእስልምና አስተምህሮዎች መርጦ፣ በሃይማኖቱ መምህራን ላይ ለመጫን ያደረገው ሙከራ ከፍተኛ ተቃውሞና ውጥረት ፈጥሮ መሰንበቱ ይታወቃል።
“ይህን ውጥረት ለማርገብ የሚያስችል አንዳችም ምልክት በመንግሥት በኩል አልተሰጠም” ብለዋል አንድ ታዋዊ የሃይማኖቱ ቃዲ ።
ይህ ውጥረት ባለበት ሁኔታ፣ በኢሕአዴግ ካድሬዎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ እንደሚመራ የሚታማው መጅሊስ፤ በአወሊያ ትምህርት ቤት አስተዳደር ጣልቃ በመግባት የፈጠረው አዲስ ቁጣ ነገሩን እንዳባባሰው በርከት ያሉ ምእመናን ያምናሉ።
ይህም ውስጥ ለውጥ ሲብላላ የቆየውን የመጅሊሱን ሕጋዊነትና ተቀባይነት ጥያቄ የአደባባይ ጥያቄ እንዲሆን አድርጎታል። በመጅሊሱ ላይ ቅሬታ ያላቸው የሃይማኖቱ ተከታዮች በተለያየ ጊዜያት ተቃውሞዋቸውን እና የመፍትሔ ሀሳባቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ለሚመለከታቸው ሁሉ ቢያቀርቡም ሰሚ ሳያገኙ መቆየታቸውን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጮች ጠቁመዋል።
በመንግስት ጣልቃ ገብነት ሁለቱን ወገኖች ለማነጋገር ለዛሬ የተያዘው ፕሮግራም ባለመሳካቱ ፤ ለመጪው የካቲት 5 ቀን በድጋሚ ቀጠሮ መያዙን ለማወቅ ተችሏል።
በመጪው አርብ በጁማ ጸሎት ላይ ተመሳሳይ ተቃውሞ በአወልያ መስጊድ ግቢ ሊኖር እንደሚችል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።