በሙስሊም መካከል ልዩነት ለመፍጠር መንግስት እየሰራ ነው ተባለ

መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ሙስሊሞች ትናንት በአወሊያ መስኪድ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ከጠዋቱ 3፡00 እስከ ቀኑ 10፡00 ሰዓት ድረስ ተሰብስበው የኮሚቴውን ሳምንታዊ ሪፖርት አድምጠዋል፡፡ በቀጣይ ከአሕባሽ፣ ከመጅሊስና ከኢህአዴግ መንግሥት ሕገወጥ ተግባር ስለሚያደርጉትም ሠላማዋ ትግልም ተወያይተዋል፡፡

ሪፖርተራችን ያነጋገራቸው አንድ የኮሚቴው አባል ከለፈው ሣምንት ጀምሮ የመንግሥት የደህንነት ሰዎች በድብቅ ከሚያደርጉብን ክትትል እና አሰርጎ ማስገባት ባሻገር ሰሞኑን በግልጽ በሰባት የተለያዩ መኪናዎች በተለያዩ ቦታዎች ለሠላማዊ ትግል ስንንቀሳቀስ እየተከታተሉን የሥነልቦና ጫና እያሳደሩብንና እያስፈራሩን ይገኛሉ ብለውናል፡፡

 ይሁን እንጂ በዚህ ጫና ውስጥ ሆነን ለጠ/ሚ ጽ/ቤት ደብዳቤ አስገብተናል፣ አቶ መለስ ያነቡታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን በማለት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት (መጅሊስ) ዛሬ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ ጦር ኃይሎች አካባቢ ከሆላንድ ኤምባሲ አቅራቢያ በሚገኘው የጽ/ቤቱ ቅጥር ጊቢ ከሁለት ሺህ ያላነሱ ሰዎችን በማሰባሰብ የድጋፍ እንቅስቃሴ ሊያደርግ ጥሪ ማስተላለፉን ሪፖርተራችን ያናገራቸው የመጅሊስ የዜና ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የኢህአዴግ መንግሥት ሊዚህ ዝግጅት ድጋፉን መስጠቱን እናውቃለን ያሉን አንድ ሆላንድ ኤምባሲ አካባቢ የሚገኘው የሸሆ ጀሌ መስኪድ ኢማም ጥሪው እየተላለፈ ያለውም በተንቀሳቃሽ፣ በቤትና በቢሮ ስልክ፣ ሰው ለሰው ባለው የግንኙነት መረብ እና የመጅሊስ ደጋፊና ተባባሪ ይሆናሉ ተብለው የሚታሰቡ የኢህአዴግ አባላት ሙስሊሞችና የአህባሽ ሰዎች ናቸው ብለዋል፡፡

የመጅሊስ ሰዎች ገና ለገና በእነርሱና በመንግሥት ጫና ሥር ያለ ምርጫ ይካሄዳል ብለው ውስጥ ውስጡን ሰዎችን እየመለመሉና በገንዘብ እያዘጋጁ ነው ያሉት ኢማሙ ፣ ራዲዮ ፋና  የኢትዮጵያ ራዲዮ እና ቴሌቭዥን ድርጅት እውነትን እያጣመሙ በመጅሊስና በኢህአዴግ መንግስት ጎን ያለ መረጃ ብቻ እያቀረቡ ነው  በማለት ገልጸዋል፡፡

የመንግስት እንቅስቃሴ በግልጽ ሙስሊሙን ከሁለት በመክፈል ለማጋጨት እየሰራ መሆኑን አክለው ገልጠዋል። መጅሊሱ የጠራው ስብሰባ ውጤት ዜናውን እስካጠናቀርንበት ጊዜ ድረስ አልደረሰንም።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide