በሙርሌ ታጣቂዎች ታፍነው ከተወሰዱት ህጻናት መካከል 44 የሚሆኑ መመለሳቸው ተነገረ

ኢሳት (ግንቦት 9 ፥ 2008)

ከአንድ ወር በፊት በጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን ድንበር ተሻግረው በመጡ በሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ከተጠለፉት 125 ከሚሆኑት ህጻናት ውስጥ 44 ያህሉ ትናንት ሰኞ ወደ ጋምቤላ ክልል መመለሳቸው ተገልጸ። ህጻናቱ የተመለሱት ከጠላፊዎች ጋር በተካሄደው ረጅም ጊዜ በፈጀ ድርድር እንደሆነ ሱዳን ትሪቢዩን ዘግቧል።

ከ1 እስከ 5 ዓመት እድሜ ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ህጻናት እንዲመለሱ የተደረጉት ወደ ጋምቤላ ክልል ሲሆን፣ ለአንድ ወር ያክል በታጠቁ የሙርሌ አማጽያን ታግተው መቆየታቸው ይታወቃል። ህጻናቱን ከደቡብ ሱዳን ያመጡት የኢትዮጵያ ወታደራዊ ሄሊኮፕተሮች መሆናቸውን ሱዳን ትሪቢዩን በዘገባው አክሎ አመልክቷል።

የደቡብ ሱዳን ምክትል መከላከያ ሚንስትሩ ዴቪድ ያው ያው ከክልል አስተዳደር ሃላፊዎችና በአካባቢው ከሚኖሩት የጎሳ መሪዎች ጋር በመሆን ከጠላፊዎቹ የሙርሌ ጎሳ አባላት ጋር ድርድር ሲያደርጉ እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል። በቅርቡም 32 ህጻናት ሊኳንጎሌ በሚባል አካባቢ ባሉ ሶስት መንደሮች የተለቀቁ ሲሆን በኋላም የቦማ ግዛት ርዕሰ-ከተማ ወደሆነችው ፒቦር እና ጁባ መወሰዳቸው ታውቋል። በመጨረሻም ወደ ጋምቤላ ክልል በሄሊኮፕተር መወሰዳቸውን ሱዳን ትሪቢዩን ትናንት ባወጣው ሪፖርት ዘግባል።

የቀሩትን ህጻናትና የተዘረፉትን 2 ሺ የቀንድ ከብቶች የማስመለስ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን መናገራቸው ዘገባው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት የሙርሌ ጎሳ አባላት በጋምቤላ ክልል ከ208 ወላጆችንና ከገደሉና 125 በላይ የሚሆኑ ህጻናትን ጠልፈው ከወሰዱ በኋላ ታጣቂዎችን አሳዶ ለመቅጣት ሲዝትና ህጻናቱንም በጥቂት ቀናት እንደሚያስለቅቅ ለመገናኛ ብዙሃን መናገሩ አይዘነጋም።  ሆኖም፣ የፌዴራል ኮሚውኒኬሽን ሚንስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ በሉዓላዊ አገር ደቡብ ሱዳን ውስጥ ገብተን ጦርንት ስናደርግ፣ የዚያችን ሉዓላዊ አገር እውቅናና ይሁንታ ልናገኝ ይገባል ማለታቸው ታውቋል።