ግንቦት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በባህር ዳር ከተማ በመሸንቲ ሳተላይት ቀበሌ ቆጥቆጥማ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ግንቦት 1/2005 ዓ/ም ሁለት መኪናዎች ተጋጭተው የ16 ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ማለፉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
አደጋው የተከሰተው ከእንጅባራ ወደ ባህር ዳር ከተማ 19 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-08862 አማ የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ ከባህር ዳር ከተማ ወደ ዳንግላ ከተማ በመጎዝ ላይ ካለ ንብረትነቱ የአማራ ውሃ ስረዎች ኮንስትራክሽን የሆነ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-0239 አማ የጭንት መኪና ጋር በመጋጨቱ ነው፡፡
አደጋው የደረሰው ከረፋዱ 3፡30 ሲሆን በከፍተኛ ፍጥነት ላይ በመጓዝ ላይ የነበረው የሚኒባስ የፊት ጎማ ፈንድቶ ከፊት ለፊት ከሚመጣው የጭነት መኪና ጋር በመላተሙ ነው፡፡
የ16 ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው 3 ሰዎች ደግሞ በባህር ዳር ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል ተኝተው ህክምና እየተደረገላቸው ባለበት ወቅት የአንድ ሰው ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ በድምሩ 17 ሰዎች ህይዎታቸውን ማጣታቸውን የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማረጋገጫ ዋና የስራ ሂደት የስልጠናና ትምህርት ኦፊሰር ኢንስፔክተር ሙሉጌታ በዜ ገል ጸዋል፡፡
አደጋው እጅግ አሰቃቂ መሆኑን የገለጹት ኦፊሰሩ ሁለት የቤተሰብ አባላት ወንድማማቾች ህይዎታቸው ካለፉት ውስጥ እንደሚገኙበት ገልጸዋል ፡፡
በከባድ መኪናው ውስጥ የነበሩና ጉዳት የደረሰባቸው ሁለት ግለሰቦች ደግሞ የመጀመሪያ እርዳታ ተደርጎላቸው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን አስታውቀወል፡፡
አንድ የአይን እማኝ አደጋው አሳቃቂ እንደነበርና ተሰፋሪዎች ሰዎነታቸው ተቆራርጦ መገኘቱን ተናግሯል
በኢትዮጵያ የመኪና አደጋ ከኤች አይ ቪ ኤድስ በመቀጠል ለሺዎች ሞት ዋና ምክንያት እየሆነ ነው።