ኢሳት (ሰኔ 21 ፥ 2008)
የእንግሊዝ ፖሊስ ከኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ኤርትራ የፈለሱ 28 ስደተኞችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።
በእቃ መጫኛ መኪና ውስጥ የተገኙት እነዚህ ስደተኞች አስራ አንዱ ኤርትራውያን፣ አስሩ ሱዳናውያን ሰባቱ ደግሞ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ዴይሊ ሜይል የተባለ በእግሊዝ አገር የሚታተመው ጋዜጣ ማክሰኞ ባወጣው ዘገባ አመልክቷል።
በእቃ መጫኛ ከባድ መኪና ታጭቀው ከተገኙት ከእነዚሁ ስደተኞች መካከል ህጻናትና ሴቶች ይገኙበታል ተብሏል። ስደተኞቹ መጸዳጃ ቤት ለመጠቀም ፖርስትማውዝ በተባለ ቦታ በመቆማቸውና ለፖሊስ ጥቆማ በመድረሱ ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል ተብሏል።
በአካባቢው የእሳት አደጋ መኪናዎች፣ አምቡላንሶችና የስደተኞች ጉዳይ ሃላፊዎች በመምጣታቸው ትርምስ ተፈጥሯል ሲል ዴይሊ ሜይል ጋዜጣ በዘገባው አክሎ ገልጿል።
ስደተኞቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ አንድ ሰው ወደ ሆስፒታሉ የተወሰዱ ሲሆን፣ ሌላ ህጻን የማህበራዊ አገልግሎት እንክብካቤ እየተሰጠው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
የእንግሊዝ ድንበር ጠበቂዎች ከፍተኛ ቅኝትና ቁጥጥር ቢያደርጉም፣ ብዛት ያላቸው ስደተኞች አሁንም ወደ አገሪቷ እየጎረፉ እንደሚገኙ የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
እንግሊዝ በቅርቡ ከአውሮፓ ህብረት የተለየችበት ዋነኛው ምክንያትም ይኸው የስደተኞች ጉዳይ እንደሆነ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ ቢቆዩም የአውሮፓ ህብረት አገራት ዜጎች የመዘዋወር መብትን በመጠቀም ወደእንግሊዝ እየፈለሱ በማስቸገራቸው እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት ለቃ ለመውጣት ተገዳለች ተብሏል።
ሆኖም የእንግሊዝ መንግስት ከአውሮፓ ህብረት አባላት በተለይም ከፈረንሳይ፣ ቤልጅየምና፣ ሆላንድ ጋር በመተባበር የሰው አዘዋዋሪ መረብ ለመበጣጠስና ህወገጥ ፍልሰትን ለማስቆም እየሰሩ እንደሆነ ገልጿል።