ኢሳት (መጋቢት 28 ፥ 2008)
በሃገር መካላከያ ሰራዊት ውስጥ ሰራዊት ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ለብቻቸው እየተጠሩ ገንዘብ እንዲያዋጡ መጠየቃቸው የመከላከያ ሚኒስቴር ምንጮች ለኢሳት ገለጹ። በሁሉም የጦር ክፍሎች እንዲካሄድ ከበላይ ወረደ በተባለ ትዕዛዝ መሰረት በዚሁ ሳምንት በሁመራ ግንባር ስብሰባው መካሄዱንም መረዳት ተችሏል።
በሁመራ ግንባር በሚገኘው 5ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ለብቻቸው ተጠርተው፣ የትግራይን ህዝብ ተጋድሎ የሚያሳየው ፊልምና መጽሃፍ ገንዘብ እንዲያዋጡ ተጠይቀዋል።
በስብሰባው ውስጥ የነበሩት አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች ለብቻቸው የተደረገላቸውን ጥሪ የተቃወሙ ሲሆን የሌላው ኢትዮጵያዊ ተጋድሎስ በማለት መጠየቃቸው ተመልክቷል።
ከሰራዊቱ አባላት ለሚነሳው ጥያቄ ምላሽ መስጠት የተሳናቸው የስብሰባው መሪዎች፣ የበላይ አካል ትዕዛዝ ስለሆነ እኛ መለወጥ አንችልም በማለት ማሰናበታቸውም ተመልክቷል።
የትግራይ ህዝብ ተጋድሎ ያሳያል የተባለው ፊልም እንዲሁም መጽሃፍ በማን እንደተዘጋጀና መቼ ለእይታ እንደሚበቃ የታወቀ ነገር የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የበታች ሹማምንትና መኮንኖች ያሳተፈ ስብሰባ በሁሉም የጦር ክፍሎች እንዳካሄደ ከበላይ አካል ትዕዛዝ መወርዱ ታዉቋል። በሃገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ለመወያየት በሚል የተዘጋጀው ስብሰባ በአንዳንድ ጦር ክፍሎች ቀደም ሲል የተጀመረ ሲሆን፣ በሌሎችም እንደሚቀጥል የመከላከያ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።