በመከላከያ ሰራዊት ፊት ኢሳዎች በአፋሮች ላይየሚፈጽሙት ግፍ ልኩን አልፏል ሲል የአፋር ፎረም አስታወቀ

ሰኔ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ፎረሙ ለኢሳት በላከው መግለጫ ካለፈው ወር ጀምሮ በሶማሊ ክልል መንግስት የሚደገፉ ታጣቂ ሚሊሻዎች በአፋር ተወላጆች ላይ ግድያ እየፈጸሙ ነው። የመከላከያ ሰራዊት አባላት ቆመው እየተመለከቱ በርካታ አፍር ወጣቶች መገደላቸውን ፎረሙ ጠቅሷል።

ፎረሙ የጅቡቲ መንግስት ለኢሳ ታጣቂዎች ድጋፍ እየሰጠ ነው በሚልም ክስ አቅርቧል። በሶማሊያ ክልል የሚደገፉት ኢሳዎች የመሬትና የኢኮኖሚ ጥያቄ አለን እንደሚሉ የጠቀሰው ፎረሙ፣ ለዘመናት ተከባብረው የኖሩት የአፋርና የኢሳ ተወላጆች እንዲጋጩ እየተደረገ ያለው መንግስት እድሜውን ለማራዘምና የራሱን ጥቅም ለማስከበር በሁለቱ አካባቢዎች በሚፈጥረው ግጭት ምክንያት ነው ሲል አክሎአል።

በአፋር ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ የሶማሊ ክልል፣ የጅቡቲ መንግስትና ኢትዮጵያ መንግስት እንዲያስቆሙ ጠይቋል። የኢትዮጵያ መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአፋር የሚታየውን የጽጥታ መደፍረስ ለማስቆም በሚል ሰበብ ሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ሲፈጽም መቆየቱን መዘገባችን ይታወሳል። ከስኳር ልማት ጋር በተያያዘ በመንግስትና በአፋር ህዝብ መካከል አለመግባባት መስፈኑንም መዘገባችን ይታወቃል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide