በመከላከያ ሰራዊት ርምጃ በኦሮሚያ ክልል ሰላማዊ ሰዎች እየተገደሉ መሆናቸው ቁጣን ቀሰቀሰ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 20/2010)በመከላከያ ሰራዊት ርምጃ በኦሮሚያ ክልል ሰላማዊ ሰዎች እየተገደሉ መሆናቸው በነቀምት ከተማ የሕዝብ ቁጣን እየቀሰቀሰ መሆኑ ተነገረ።

በኦሮሚያ በአንድ ሳምንት ብቻ 30 ሰዎች ሲገደሉ 37 ደግሞ ቆስለዋል።

በአምቦ የመከላከያ ሰራዊት በሕዝብ ላይ በከፈተው ተኩስ ግንባራቸውንና ልባቸውን ተመተው የተገደሉ መኖራቸውን የከተማዋ ኮሚኒኬሽን ሃላፊ ገልጸዋል።

በነቀምት በተነሳ ሕዝባዊ ተቃውሞም 3 ሰዎች በአካባቢው ነዋሪዎች መገደላቸው ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የትግራይ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ በኦሮሚያ አስተዳደር ስር የሚመራውን የኦሮሞ ብሮድካስት ኔትወርክ የዘረኝነት ዘገባ እያቀረበ ነው ሲል ከድርጊቱ እንዲታቀብ አስጠንቅቋል።

ድርጊቱን ካላቆመ ግን የአጸፋ ርምጃ እኛም በሚዲያ እንጀምራለን በማለት የትግራይ አስተዳደር አሳስቧል።

በአምቦ ከተማ ከአራት ቀናት በፊት በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ ከ10 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ሰሞኑን መገለጹ ይታወሳል።

ይህን ርምጃ የወሰዱት ደግሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መሆናቸውን የአምቦ ከተማ ኮሚኒኬሽን ሃላፊ አቶ ጋዲሳ ደሳለኝ ድፍረት በተሞላበት ሁኔታ በድጋሚ አረጋግጠዋል።

ሃላፊው ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለጹት የከተማው የጸጥታና የፖሊስ አካላት የመከላከያ ሃይል ከመምጣቱ በፊት ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት እያደረጉ ነበር።

ይህ ባለበት ሁኔታ ግን የመከላከያ ሰራዊት ከጉደርና አዲስ አበባ አቅጣጫ በመምጣት በከተማው ሕዝብ ላይ ተኩስ ከፍቷል ነው ያሉት።

እናም በአንድ ክሊኒክ ብቻ ህክምና ካገኙ 16 ሰዎች 15ቱ በጥይት የተመቱ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ከነዚህም መካከል ሁለቱ ሕይወታቸው ያለፈው አንዱ ግንባሩ ላይ ሌላው ደግሞ ልቡ ላይ በመከላከያ ጥይት ተመተው እንደሆነ ነው የገለጹት።

ሌሎች 23 የአካል ጉዳት የደረሰባቸውም በአምቦ ሆስፒታልና በግል ክሊኒኮች መታከማቸውንና ሁሉም በመከላከያ ሰራዊት የተመቱ ናቸው ነው ያሉት።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በነቀምት ከተማ ግጭት ተቀስቅሶ 3 ሰዎች በአካባቢው ነዋሪዎች መገደላቸው ተነግሯል።

የኦሮሚያው ግጭት በተባባሰበት ሁኔታ የትግራይ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ የኦሮሚያ ብሮድካስት ኔትወርክ/ኦ ቢ ኤን/ ዘረኛ ዘገባ እየሰራ ነው ሲል አስጠንቅቋል።

እናም ቢሮው ለብሮድካስት ባለስልጣን በጻፈው ደብዳቤ የኦሮሚያ ብሮድካስት ኔትወርክ በሕግ እንዲጠየቅለት አሳስቧል።

ይህ የማይሆን ከሆነ ግን እኛም በራሳችን ሚዲያዎች ወደ ማውገዝ እንሸጋገራለን ብለዋል የትግራይ ኮሚኒኬሽኝ ቢሮ ሃላፊ አቶ ገብረሚካኤል መለስ።

በኦሮሚያ ያለውን ግጭት የሕወሃት አባላት ከጀርባ ሆነው እያባባሱት መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ይህንንም የኦሮሚያ ሚዲያ በመዘገቡ የትግራይ ኮሚኒኬሽን ቢሮን አበሳጭቷል።

አሁን ባለው ሁኔታም በነቀምት ከተማ ፍንዳታ መሰማቱንና አንድ ባጃጅ መቃጠሉ ተነግሯል።