የካቲት ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ምንጮች እንደሚሉት በድሬዳዋ የተጀመረው በመንግስት የሚደገፈው የሙስሊም መሪዎች ግምገማ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ይልቅ ፖለቲካዊ ይዘቱ አመዝኖ ታይቷል። ከየክልሉ ተወክለው የመጡት መሪዎች አንዱ ሌላውን እንዲገልጽ በማስገደድ ጭቅጭቆች መፈጠራቸውንም ለማወቅ ተችሎአል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አክራሪነትን ለመቋቋም በሚል ህዝባዊ ንቅናቄ እንደሚጀምር አስታውቋል። በዚህ ንቅናቄ የሃይማኖትና ፖለቲካ አክራሪዎችን በየቀበሌው ያለውን ህዝብ በመሳተፍ ለመወጋት ማቀዳቸውን የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም ተናግረዋል።
እስከዛሬ የወጡት እቅዶች ውጤት አልባ መሆናቸው መንግስት በየጊዜው አዳዲስ እቅዶችን ለማውጣት ተገዷል። የአሁኑ እቅድ የአንድ ለአምስት አደረጃጀትን በመጠቀም ህዝቡ አክራሪ ሃይማኖተኛና ፖለቲካኞችን አጋልጦ በማውጣት ለመንግስት በማስረከብ እርምጃ ያስወስዳል። አንድ ሰው አክራሪ ሃይማኖተኛ ወይም አክራሪ ፖለቲከኛ መሆኑ የሚታወቀው በቀበሌው ህዝብ መሆኑ ፣ አሰራሩ በህብረተሰቡ ውስጥ የእርስ በርስ ግጭት ሊያስከትል የሚችልበት እድል ሰፊ ነው ሲል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።