ጥቅምት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአዲስ አበባ መስተዳድር ስር ባሉ የመንግስት መ/ቤት ውስጥ የሚገኙ የብአዴን አባላትና ደጋፊዎች ስለ ብአዴን የትግል ታሪክ እና ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ለኢህአዴግ እያደረገ ስላለው አስተዋጽኦ፣ ከዚህ ቀደም ብአዴን ስላበረከተው ድርጅታዊ አስተዋጽኦ እንዲሁም የክልሉ ህዝብ ለድርጅቱ ያበረከተው አስተዋጽኦ የጎላ ነበር የሚል አጠቃላይ ይዘት ያለው እውቅና ለመስጠት በሚል የተዘጋጀውን ከተማ አቀፍ ድግስ የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽ/ቤት ከሁሉም የመንግስት መ/ቤቶች በጀት ላይ በመቀናነስ እንዲሸፈን ማድረጉን የመስተዳድሩ ምንጮች ገልጹ፡፡
ከዝግጅቱ ጋር በተያያዘም በከተማዋ የተለያዩ ዋና ዋና አደባባዮች ላይ የብአዴን አርማን በመስቀል እስከ ህዳር 11 ድረስ ሳይነሳ እንዲቆይ የሚደረግ ሲሆን፣ በተለይ ግን የበጀት ወጪውን በተመለከተ ከመንግስት ካዝና የሚወጣ መሆኑን ለማስተባበል ያመች ዘንድ ከነጋዴው ህብረተሰብ የመዋጮ ገንዘብ ተሰብስቦ እንደተሸፈነ አድርጎ ለህዝቡ ለማቅረብ የወረዳ ካድሬዎችን ለገንዘብ ስብሰባ አሰማርቷል።
“የንግዱ ማህበረሰብ ለድርጅቱ ቲሸርት መግዣ ገንዘብ አናዋጣም፣ ይልቁን በዚህ ወቅት በድርቅ ለተቸገሩ ዜጎች አዋጡ ብትሉን ይሻላል” የሚል ምላሽ እየሰጠ መሆኑን የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል።
ነጋዴዎቹ ” በድርቅ የተቸገሩ ዜጎችን ቁጥርን በማሳነስእና መንግስትም በአፋጣኝ ምላሽ እንደሰጠ አድርጋችሁ በማውራት ችግሩን ለማድበስበስ እየሞከራችሁ ነው” በሚል ጥያቄ እያቀረቡ ሲሆን ፣ በኢሳት የሚቀርበው የተራበው ህዝብ ቁጥር እና እናንተ የምትገልጹት ባለመጣጣሙ እውነቱን ንገሩን በማለት ነጋዴዎች ሳይፈሩ መጠየቃቸውን የአዲስ አበባ ካድሬዎች ያሰባሰቡት መረጃ አመልክቷል።
ነጋዴዎቹ ” ከቻላችሁ በድርቅ ለተጎዱት ወገኖች ገንዘብ የምናዋጣበትን መንገድ አመቻቹ” የሚል ምላሽ በየቦታው መስጠታቸው፣ የብአዴን ሹሞችን አበሳጭቷል።