(ኢሳት ዜና–መስከረም 12/2010) በኢትዮጵያ ባለፉት 10 አመታት በመንገድ ግንባታና ስርጭት ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ግንባር ቀደም ሆና የተገኘችው ትግራይ መሆኗን የአለም ባንክ ጥናት አመለከተ።
አማራ ክልል ደግሞ የመጨረሻ ሆኖ ተመዝግቧል።
ለመንገድና ለልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች በስልጣን ላይ ላለው የኢትዮጵያ መንግስት በብድርና በስጦታ ገንዘብ በማቅረብ የሚታወቀው የአለም ባንክ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 10 አመታት የተካሄዱ የመንገድ ግንባታዎችን የገመገመበትን ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።
አዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ የመንገድ ስርጭት የታየባቸው ሲሆኑ ክክልሎች ደግሞ የትግራይ ክልል ከፍተኛ የመንገድ ስርጭት ተመዝግቦበታል።
እንደ አውሮፓውያኑ ከ2006 እስከ 2016 ከክልሎች የመንገድ ስርጭት የመጨረሻ ሆኖ የተመዘገበው የአማራ ክልል እንደሆነም ታውቋል።
በአጠቃላይ በሀገሪቱ ገጠሮች የመንገድ ስርጭት ደካማ እንደሆነም ተመልክቷል።
በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገቱ መቀጠሉን የሚናገረው የአለም ባንክ እድገቱ በዋናነት በግብርናና በአገልግሎት መስክ መሆኑን ያብራራል።
ሆኖም የድሃና ሃብታሙ ርቀት እንደሰፋ መቀጠሉን በድህነት ደረጃ ላይ ያሉ ዜጎች ቁጥር ይበልጥ እያሻቀበ መሄዱንም በሪፖርቱ አስፍሯል።
ከእድገቱ ጋር ተያይዞ መታየት የነበረበት የከተሞች መስፋፋትና እድገት ብዙም ልዩነት እንዳልታየበት በምሽት በሳተላይት የተነሱ ፎቶግራፎችን በአስረጅነት ያስቀምጣል።
በዚህም ከኢትዮጵያ ከተሞች መቀሌ በብርሃን ድምቀትም ሆነ የብርሃን ስፋቱ በመጨመር ቀዳሚ ሆና ስትመዘገብ ጎንደር የመጨረሻ ሆና ተመዝግባለች።
በቀድሞ መንግስት ከአዲስ አበባና አስመራ ቀጥላ በሶስተኛ ከተማነት ትጠቀስ የነበረችው ድሬደዋ ከመቀሌ በእጅጉ ዝቅ ብላ ተገኝታለች።