ኅዳር ፳፪ (ሃያ ሁለት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የምስራቅ አፍሪካ አገራት ስደተኞች ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በእርስበርስ ጦርነት ወደምትታመሰው የመን በብዛት እየገቡ ነው። አስተማማኝ ባልሆኑ ጀልባዎች ተጭነው የመን የገቡ ኢትዮጵያዊያን እና ሶማሊያዊያን ስደተኞች በያዝነው ዓመት ብቻ ከመቶ ሽህ መብለጡን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳውቋል።
እስካሁን ድረስ ቁጥራቸው ከ90 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን እና ከ17 ሽህ በላይ ሶማሊያዊያን ዜጎች ከሞት አደጋ ተርፈው በሰላም ወደ የመን እና የባሕረሰላጤው አገራት መግባታቸውን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ በሪፖርቱ አመላክቷል። በድርጅቱ የስደተኞች ጉዳይ ሃላፊ የሆኑት ዊሊያም ስፒንድለር ከጄኔቫ እንዳሉት ”ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ወደ ገልፍ አገራት የሚመጡ ስደተኞች ስለ የመን ወቅታዊ ሁኔታ የተዛባ የሃሰት መረጃዎች ሳይነገራቸው አይቀርም” ብለዋል።
ዊሊያም ስፒንድለር አክለውም በየመን ያለው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ተባብሶ ቢቀጥልም ኢትዮጵያዊያን እና ሶማሊያዊያን ስደተኞች ግን በአገራቸው ያለውን ሰላም ማጣት፣ ድህነት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመስጋት አሁንም በገፍ መፍለሳቸውን አላቋረጡም። ይህም ሁኔታውን ይበልጥ ውስብስብ እያደረገው መምጣቱን አስረድተዋል።
በየመን በተቀሰቀሰው የእርስበርስ ጦርነት ሳቢያ ከ3 ሚሊዮን በላይ የአገሪቱ ዜጎች መኖሪያ ቀያቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት አገራት የተሰደዱ ሲሆን ቁጥራቸው ከ7 ሽህ በላይ የሚሆኑ ሰላማዊ ንጹሃን ዜጎች ደግሞ የማትተካ ሕይወታቸውን አጥተዋል። እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ መግለጫ ወደ የመን በጀልባ ከሚገቡት ውስጥ በቅርቡ 79 ያህሉ ስደተኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል። አብዛሃኞቹ ስደተኞች የተለያዩ አካላዊ እና ወሲባዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጥቃቶች ይፈጸሙባቸዋል።
ባለፈው ዓመት እ.ኤ አ. 2015 ከ92 ሽህ በላይ ስደተኞች በተመሳሳይ ባህር አቆራርጠው ወደ ባህረሰላጤው አገራት መግባታቸውንም አልጀዚራ አክሎ ዘግቧል።