ግንቦት ፴ ( ሠላሳ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአማራ ክልል እግር ኳስ ፊዴሬሽን የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፊድሬሽን ያስተላለፈውን ውሳኔ አውግዟል፡፡ ውሳኔው ህግና ስርዓቱን ያልተከተለና ለመቀሌ ያደላ ነው ያለው የአማራ ክልል እግር ኳስ ፊዴሬሽን ፥ ፊዴሬሽኑ ያሳለፈው ውሳኔ በተፅኖ ነው ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡ የጣናው ሞገድ የባህር ዳር ከነማ ስራ አሰፈፃሚዎች በበኩላቸው ከዚህ በኃላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብለን ለመጥራት ይቸግረናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን በጣናው ሞገድ ባህር ዳር ከነማ ላይ ያሳለፈው የጥፋተኝነት እና ለመቀሌ ከነማ የተላለፈው የደጋፊዎቻችሁን አሰልጥኑ ውሳኔ፥ ዝርዝር አንቀፆችን የሻረ እና አንዱን ክለብ ተደጋጋሚ ጥፋት ሲፈፅም እሹሩሩ በማለት ላይ የተመሰረተ መሆኑን የክልሉ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስታውቋል።
አቶ አብርሃም ገነቱ የአማራ ክልል እግር ኳስ ፊድሬሽን ፕሬዝዳንት ፣ የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ስፖርት አካዳሚ ረዳት ፕሮፌሰር ደምስ ፣ አቶ ማርሸት ዳኘው የባህር ዳር ከነማ ስራ አስፈፃሚ እና የጣናው ሞገድ ደጋፊ ወጣት ገረመው አባተ በሰጡት አሰተያየት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፊድሬሽን ያሳለፈው ውሳኔ መቀሌን የፈራ ከመሆኑም በላይ ችግሮችን የማረም ብቃቱ ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፊድሬሽን በ2009 ዓ.ም በወጣው የዲስፕሊን መመሪያ አንቀፅ72 ተራ ቁጥር 4 መሰረት የተጋጣሚ ቡድን ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ከገቡ እና ጭዋታው ከተቋረጠ ጭዋታው በፎርፌ ከመሰጠቱም በላይ ፎርፌየተሰጠበት ቡድን ከ2-9 ነጥብ ይቀነስበታል፡፡ ከ50 እስከ 100 ሽህ ብር ይቀጣልም፡፡ በዚሁ ላይ ከአንድ እስከ ሁለት አመት በሜዳው የሚደረግ ጨዋታ ይታገዳል፡፡
ፌድሬሽኑ ይህን ህግ ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ በራስ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እና ተደጋጋሚ ጥፋት እየፈፀመ ያለውን መቀሌ ከነማ ተሸክሞ ሲጓዝ ይታያል ይላሉ፡፡በተደጋጋሚ ችግር የሚፈጥርን ቡድን እሹሩሩ ማለት አልገባንም የሚሉት ባህር ዳር ከነማዎች ፣ የባህር ዳር ከነማ መጎዳቱ እየታወቀ አላስፈላጊ ውሳኔ ተላልፎብናል ብለዋል፡፡
ለመቀሌ ከነማ የተላላፈው የክለብ ግዴታ የሆነውን ደጋፊዎችን የ20 ቀናት ስልጠና መስጠት እንደቅጣት አድርጎ ማስተላለፍ ቀልድ ነው ብለውታል፡፡ እኛ ከዚህ ሁሉ በደል በኃላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፊድሬሽን ልንለው አንችልም ያሉት ባህር ዳር ከነማዎች ፥ መመሪያው ለአንዱ ይሰራል ፤ ለአንደኛው አይሰራም ብለዋል፡፡
ነገሩ አሁን ከእግር ኳሱ አልፎ ህዝብን እና ህዝብን የሚያተራምስ ተግባር እየሆነና የፖለቲካዊ ይዘት እየያዘ ነው ሲሉ የአማራ ክልል እግር ኳስ ፊድሬሽን ፕሬዝዳንት ተናግረዋል፡፡
በሰዓቱ የተከሰተውን ዘግናኝ አጋጣሚ እንዲባባስ እያደረገ ያለው ባህር ዳርን ሲቀጣ 24 ስዓታት ያልወሰደበት ፊድሬሽኑ ነው ብለዋልም፡፡