(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 5/2010)በመቀሌ ከተማ ያለውን የውሃ እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት የፌደራል መንግስት ከቻይና መንግስት ባገኘው 8 ቢሊየን ብር የግድብ ግንባታ እንደሚጀምር ተገለጸ።
የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅም ለከተማዋ ከሚያስፈልገው የውሃ መጠን ከሁለት እጥፍ በላይ ተጨማሪ ውሃ እንደሚያስገኝም ተመልክቷል።
የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕወሃት/ ንብረት የሆነው ሬዲዮ ፋና እንደዘገበው የመቀሌ ከተማ በየቀኑ የሚያስፈልገው 50ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ ቢሆንም እየቀረበ ያለው ግማሽ ያህሉ 25ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ ነው።
ችግሩን ለመፍታት የክልሉ መንግስት እያደረገ ባለው ጥረት ተጨማሪ 18ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ የሚያስገኝ ግድብ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
ይህም ሆኖ የከተማዋን የውሃ ፍላጎት ለማርካት ተጨማሪ 7ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ የሚያስፈልግ በመሆኑ ከቻይና መንግስት በተገኘ 8 ቢሊየን ብር ተጨማሪ ግድብ ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን የትግራይ ክልል ውሃ ሃብት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ተስፋ ሚካኤል ገብረዮሐንስ ገልጸዋል።
የፌደራል መንግስቱ ከቻይና ተበድሮ ለትግራይ ክልል በሚሰጠው 8 ቢሊየን ብር ተጨማሪ 147 ሺ ሜትር ኪዩብ የመጠጥ ውሃ በቀን እንደሚመነጭም ተመልክቷል።
በዚህም በአጠቃላይ በትግራይ በቀን የሚመነጨው የመጠጥ ውሃ ከፍላጎቱ በ140 ሺ ሜትር ኪዩብ ብልጫ እንደሚኖረውም ተመልክቷል።
በርዕሰ መዲናዋ አዲስ አበባ ወደ 4 ሚሊየን ሕዝብ በመጠጥ ውሃ በሚቸገርበት ወቅት የፌደራል መንግስት 8 ቢሊዮን ብር ተበድሮ በአሁኑ ወቅት 220ሺ ነዋሪ ላላት መቀሌ ከተማ ቅድሚያ መሰጠቱ በምን ምክንያት እንደሆነ አልታወቀም።
በውሃ ጉዳዮች ላይ ጥናት የሚያደርገው water.org ባደረገው ጥናት ከኢትዮጵያ 100 ሚሊየን ሕዝብ ውስጥ 61 ሚሊየን የሚሆነው የንጹህ መጠጥ ውሃ እንደማያገኝ አረጋግጧል።