በመርሃቤቴና በመንዝ ወረዳዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጋዮች ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሱ የዞኑ ፖሊስ አመነ

ሚያዝያ ፬ (አራት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአማራ ክልል በሰሜን ሽዋ ዞን በመርሃ ቤቴና በመንዝ ቀያ ወረዳዎች በመዘዋወር ለነጻነታቸው ሲዋጉ የተሰውት ሁለቱ የነጻነት ታጋዮች ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አምኗል።
በነበሩ ከመሰለውና ጭንቅል አስጨናቂ የተባሉት የነጻነት ታጋዮች ፣ በገዢው ፓርቲ አመራሮች ላይ እርምጃ በመውሰድ ለገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ራስ ምታት ሆነው ነበር። ታጋዮቹ በደቡብ ወሎ ዞን ወረኢሉ ወረዳ ሚያዚያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጣሴ ጊዮርጊስ ተብሎ በሚጠራ ቦታ ላይ ከፀረ ሽምቅ ሀይሎች ጋር በተካሄደ የ1 ሰዓት የተኩስ ልውውጥ ተሰውተዋል ፡፡ በተኩስ ልውውጡ በርካታ የሽምቅ ሃይል አባላት ህይዎታቸው ማለፉም ታውቛል። ተዋጊዎቹ ለ1 አመት ያህል በመርሃ ቤቴና አጎራባች ወረዳዎች ሲንቀሳቀሱ ፣ ከ7 በላይ የኢህአዴግ አመራሮች የገደሉ ሲሆን በርካታ ንብረትም አውድመዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በኢሳት እንደተዘገበው ታጋዮቹ መንገድ ላይ መኪኖችን አስቁመው በኢህአዴግ ባለስልጣናት ላይ እርምጃ ወስደዋል።