በመራዊ የፌደራል ፖሊሶች ወጣቶችን አፍነው ወሰዱ

ኀዳር ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የፌደራል ፖሊስ እና የደህንነት ሃይሎች ከባህርዳር ከተማ በስተደቡብ በ35 ኪሜትር ርቀት ላይ በምትገኘዋ መራዊ ከተማ በመገኘት የከተማዋን ወጣቶችንና ነዋሪዎችን ከሌሊቱ አስራ አንድ ሰአት ላይ እየደበደቡ አፍነው ወስደዋቸዋል።
የሰማያዊ ፓርቲ አባላት አቶ መኳንንት ጸጋዬን እና አቶ እያዩ መጣን ጨምሮ አእምሮ መጣ፣ ሽባባው የኔአለምና አብርሃ ተሰራ የተባሉ ነዋሪዎች ታስረዋል።የፌደራል ፖሊስ አባላት በአካባቢው የሚያደርጉትን አሰሳ በመቀጠላቸው፣ በርካታ ወጣቶች ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል መሰወራቸው ታውቋል። በሌሊት የተያዙት ወጣቶች ከፍተኛ ድብደባ የደረሰባቸው ሲሆን፣ በአሁኑ ሰአት ባህርዳር ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ታውቋል።
ከአሁን በፊት መምህር ስማቸው ምንይችል፣ ደህናሁን ቤዛን ጨምሮ ከ30 ያላነሱ የመራዊ ከተማና የሜጫ ወረዳ ወጣቶች እየታፈሱ ተወስደው ታስረዋል። በከተማዋና በወረዳው የደህንነት ሃይሎች በብዛት ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን፣ የወረዳው ወጣቶች በስርዓቱ ደስተኛ ባለመሆን ለውጥ መፈለጋቸው ስርዓቱን እንቅልፍ እንደነሳው ወጣቶች ይገልጻሉ። አቶ መኳንት ፀጋየ የታዳጊ ልጆቹን ስነልቦና በሚጎዳ መልኩ በቤተሰቡ ፊት ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞበታል። ቀድም ብሎም መንግስትን አትደግፍም በመባሉ በተለያዩ ጊዜያት ከስራ ታግዶ ቆይቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ በደቡብ ጎንደር የደልጊ ነዋሪዎች በፌደራል ፖሊሶች ታፍነው ተወስደዋል። ታፍነው ከተወሰዱት መካከል አቶ አሰፋ ገዳሙ፣ ወታት አዲሱ አያሌው፣ አቹ ወርቁና ሙሉጌታ ክፍሌ ይገኙበታል።