የካቲት ፳፫ ( ሃያ ሦስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአገሪቱ የተከሰተውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማስቆም ከፍተኛ ገንዘብ ወጭ በማድረጉ በዚህ አመት ለመንግስት ተቋማት የስራ ማስኬያጃ የሚውል ከፍተኛ የበጀት መዋዥቅ እንደገጠመው የገንዘብ እና የኢኮኖሚ ትብብር ሚንስትር ገለፀ፡፡ በዚህም የተነሳ በኦሮምያና በአማራ ክልሎች የመስክ ስራዎች እየተቋረጡ ነው።
የሚንስትሩ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ካህሳይ ባህታ ፣ በአማራ እና ኦሮምያ ክልሎች በተካሄዱ ህዝባዊ ንቅናቄዎች ፀጥታ ለማስፈን ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የሚሊሺያ እና የወታደር ሃይል ከድንበር እና ከገጠር በማምጣት ግጭቱ በተነሳባቸውም ሆነ ባልተነሳባቸው አካባቢዎች አስፍረን በመቀለባችን የወረዳዎችን በጀት አናግቷል፤ የክልሎችም የስራ ማስኬጃ በጀት ከፍተኛ መቃወስ ገጥሞታል” ብለዋል።