ጥቅምት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-1433ኛውን የኢድ አል አደሃ በአልን ምክንያት በማድረግ በመላው አገሪቱ የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ኢህአዴግ መራሹ መንግስት እየተከተለ ያለውን ፖሊሲ በመቃወም ድምጻቸውን አሰምተዋል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም ፣ በሀረር፣ በደሴ፣ አዳማ እና ሌሎችም አካባቢዎች የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጽህፈት ወይም መጅሊስ ተወካዮች ንግግር ለማድረግ ሳይችሉ ቀርተወዋል። በተለያዩ ከተሞች በርካታ ሙስሊም ወጣቶች እየታፈሱ መታሰራቸውም ታውቋል።
በአዲስ አበባና በአካባቢው የሚገኙ ሙስሊሞች በስታዲየም በሚደረገው የአረፋ የስግደት ዝግጅት ላይ ለመሳተፍ ከማለዳው 12 ሰአት ጀምሮ ወደ ስፍራው የጎረፉ ሲሆን፣ የአንዋር መስጊድ አሰጋጅ የሆኑት ሼህ ጠሀ ሞሀመድ ሀሩን ምእመናን ምንም አይነት ተቃውሞ ሳያሰሙ ሰግደው ብቻ እንዲሄዱ ሲያሳስቡ ፣ ምእመናኑ በመቆጣት ተክቢራ በማለት ተቃውአል።
የእለቱ መርሀግብር የነበረው የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ እና የኢህአዴግ ተወካይ ሆነው የቀረቡት አቶ ሬድዋን ሁሴን እና የመጅሊስ ተወካዮች ንግግር ሊያደርጉ ሲሉ ህዝብ ሙስሊም ተቃውሞውን በመቀጠሉ መርሀ ግብሩ እንዲቋረጥ ተደርጎ ለወትሮው በ 2 ሰአት ከ30 ስአት ላይ የሚጀመረው ስግደት 2 ሰት ላይ እንዲጀመር ተደርጎ በውክቢያ መጠናቀቁን አንድ ሙስሊም በአካባቢው ለነበረው ዘገቢያችን ተናግረዋል።
የእለቱ ስግደት በፍጥነት እንደተጠናቀቀ ህዝበ ሙስሊሙ ቢጫ ካርድ አውጥቶ በማውለብለብ ለመንግስት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ያሳየ ሲሆን ፣ በድብቅ ከፍተሻ አምልጠው ያስገቡዋቸውን መፈክሮች አሰምተዋል።
“የታሰሩ የኮሚቴ አባሎቻችን በቶሎ ይፈቱ ፣ ሰሞኑን በደቡብ ወሎ ሙስሊሞችን የገደሉት ለፍርድ ይቅረቡ፣ የኢህአዴግ መንግስት መብቱን ለጠየቀው ሁሉ አሸባሪ የሚል ታፔላ አይለጥፍ፣ እኛ አሸባሪ ሳንሆን በመንግስት ተሸባሪዎች ነን፣ መጅሊስና ኢህአዴግ ያደረጉት ምርጫ ህዝብ ሙስሊሙን አይወክልም ፣ የኢህአዴግ ካድሬ የእኛ ተመራጭ ሊሆን አይችልም” የሚሉትንና እና ሌሎች መፈክሮችን በድብቅ አስገብተው አሳይተዋል።
በሁኔታው የተደናገጠው እና አስቀድሞ የተዘጋጀ የሚመስለው የፌደራል ፖሊስ ህዝበ ሙስሊሙን ከቦ ቢጠባበቅም ፣ “ፖሊስ የህዝብ አገልጋይ እንጅ የመንግስት ቅጥረኛ አይደለም” በማለት ሁኔታውን ለማብረድ የሞከሩ ሙስሊሞች ነበሩ።
የአንበሳ አውቶቡስ ያለተሳፋሪ ሙሰሊሞቹ በተሰባሰቡባቸው አካባቢዎች ሲመላለስ “መስታውት አንሰብርም፣ የፕሮፓጋንዳ አጀንዳ አንሰጥም” በማለት በሰላም እንዲያልፍ አድርገዋል።
ዘጋቢያችን እንዳለው በርካታ ሙስሊሞች ወደ ኢቲቪ በማቅናት ቢጫ ካርድ በማውለብለብ “ውሸት ሰለቸን በማለት እና አይናቸውን በመሸፈን ኢቲቪ አናይም፣ ጆሮአቸውን በመድፈን ኢቲቪን አንሰማም” በማለት የተቃወሙ ሲሆን፣ በርካታ ሙስሊም ሴቶች ወደ ኢቲቪ በመቅረብ “እኛ አሸባሪ ሳንሆን የመንግስት ተሸባሪዎች ነን፣ እውነት ዘግቡ” በማለት ተቃውመዋል።
የፌደራል ፖሊስ አባላት የደህንነት ሀይሎች እና የኢህአዴግ ካድሬዎች የበአሉ ተሳታፊዎች መበታተን ሲጀምሩ ቀንደኛ አስተባባሪ ናቸው ያሉዋቸውን በቁጥጥር ስር አውለዋል።
በደሴ ደግሞ በአብዛኛው ቦታዎች መብራት በይኖርም፣ የኢድ አልዐድሀ በዐል በሠሏት ከተከበረ
በሁዋላ መላ ሙስሊሙ ድምፁን በጋራ በማድረግ አላሁ አኩበር በማለት የባለስልጣኑን ንግግር አክሽፏል።
በሀረርም እንዲሁ ከፍተኛ ተቃውሞ በመነሳቱ መንግስት በ2 መኪኖች የተጫኑ የፌደራል ፖሊስ አባላትን በማምጣት ሀይሉን ሲያጠናክር ታይቷል።
በወልዲያም እንዲሁ ተቃውሞው በማየሉ መንግስት ተጨማሪ ሀይል ለማሰማራት ግድ ብሎት ነበር። መንግስት የመጅሊስ ምርጫ ለሁሉም ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል በሚል ችግሩን አድበስብሶ ለማለፍ ቢፈልግም ፣ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ግን ተቃውሞን በመቀጠል ላይ ነው።
ውድ ተመልካቾቻችን የዛሬውን የኢድ አል አደሀ በአል በተለመለከተ የተጠናከረውን አጭር ሪፖርት ከዜናው በሁዋላ እናቀርባለን