የካቲት ፳፩ ( ሃያ አንድ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስአበባ ከተማ የሚገኙ ነባር የሚባሉ ማስፋፊያዎች ጨምሮ ፒያሳ፣4 ኪሎ፣6 ኪሎ፣ ካዛንቺስ፣ለገሀር፣ ቂርቆስ፣ በቅሎ ቤት፣ ቦሌ፣ልደታ፣ቄራ፣ ጎተራ፣ ሳሪስ እና የመሳሰሉ አካባቢዎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን አንስቶ ወደሌላ አካባቢ የማስፈር ዕቅድ በአዲሱ ፍኖተ ካርታ (ወይም ማስተር ፕላን) መካተቱ ታውቋል።
በአዲሱ ካርታ መሰረት ከዚህ ቀደም ይደረግ የነበረውን ወደጎን የመስፋት መርህ በማስቀረት ወደላይ ማስፋት በሚል የተተካ ሲሆን ለዚህ ማስፈጸሚያ በመሀል ከተሞች ሰፋፊ ቦታዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ማስተር ፕላኑ በአዲስአበባ ከተማ በቀጣዩ 10 ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ 1 ሚሊየን 278 ሺ 418 የመኖሪያ ቤቶች ያስፈልጋሉ ያለ ሲሆን፣ ይህን ለማሟላት የቅይጥ መሬት ስትራቴጂ ማለትም በሚገነቡ ማናቸውም ሕንጻዎች የመኖሪያ ቤትን በውስጣቸው እንዲያካትቱ በማስገደድ የመኖሪያ ቤት ፍላጎትን መመለስ እንደሚቻል ያስቀምጣል፡፡ ሆኖም ሕንጻ ገንቢዎች በአስተዳደሩ ሃሳብ ላይ አስቀድመው እንዲወያዩና እንዲያምኑበት አለመደረጉ የዕቅዱ ቀጣይ ፈተና እንደሚሆን ተገምቶአል
አዲስ አበባ ካላት 52 ሺ ሄክታር ጠቅላላ የመሬት ስፋት ውስጥ 40 በመቶ ለግንባታ፣ 30 በመቶ ለአረንጓዴ ልማት፣ ቀሪው 30 በመቶ ለመሰረተ ልማት ግንባታ እንዲውል በአዲሱ ማስተር ፕላን የተቀመጠ ቢሆንም ይህን ቦታ ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ፣ ነባር ነዋሪዎችን የማንሳት እቅድ ተይዟል።
የአዲስ አበባ ከተማ ም/ቤት ሰሞኑን ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ደግሞ በከተማዋ ባለፉት ዓመታት በመልሶ ማልማት ስም የዜጎች ከይዞታቸው መናፈቀል ችግር ያለበት መሆኑን በማመን፣ አሰራሩ እንደገና እስከሚፈተሽ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲታገድ ውሳኔ አሳልፏል።
ም/ቤቱ ውሳኔውን ለማሳለፍ የተገደደው ከመሬታቸው ላይ የሚነሱ ሰዎች በየጊዜው ከካሳ አከፋፈል፣ ከምትክ ቦታ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚያነሱትን ቅሬታዎች መልስ ለመስጠት እንዲቻል መሆኑን ገልጿል። ም/ቤቱ በስብሰባው ባለፉት ዓመታት ከመሬታቸው የተፈናቀሉት ዜጎች በቂ ካሳ ባለመከፈሉ ለእንግልትና ለችግር መጋለጣቸውን፣ ተነሺዎች በቂ የመሠረተ ልማት ባልተሟሉባቸው አካባቢዎች እንዲኖሩ መገደዳቸው ስህተት እንደነበር በማመን የመልሶ ማልማት ሥራ አፈጻጸም አጥንቶ ለማስተካከል እንዲቻል ሥራው ላልተወሰኑ ጊዜያት እንዲቆም ሲል ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የአስተዳደሩ ም/ቤት ይህን ውሳኔ ሲያሳልፍ እስከዛሬ ለተፈናቀሉና ለከፍተኛ ችግር የተዳረጉ እንዲሁም ህይወታቸውን ላጡ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ካሳ ይክፈል አይክፈል የተገለጸ ነገር የለም።
በዋነኛነት የኦሮሚያን ተቃውሞ ተከትሎ እንዲሰረዝና ተሻሽሎ ወደጎን ከመስፋት ይልቅ በመሀል ከተማ ወደላይ መስፋፋትን ፕላን ያደረገው 10ኛ ረቂቅ የአዲስአበባ ከተማ ማስተር ፕላን ጸድቆ በስራ ላይ ሲውል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከመሀል ከተማ የሚያፈናቅል መሆኑ፣ ህዝቡን ከመሃል ወደ ዳር በመበታተን የፖለቲካ ተቃውሞውን ለማስቀረት የታሰበ ሊሆን እንደሚችል ዘጋቢያችን ገልጿል።
ምክር ቤቱ ቤት የማፍረስ ዘመቻው እንዲቆም ቢወስንም፣ አሁንም ቤቶችን የማፍረስ ሂደት ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ በርካታ ዜጎች መጠለያ አጥተው እስከ ልጆቻቸው እየተሰቃዩ ነው።
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ የተሰሩ የኮንዶሚኒየም ቤቶች አብዛኞቹ በህወሃት አባላት ደላሎች እየተቸበቸቡ ነው። መስተዳድሩ ለተወሰኑ ቤቶች ብቻ እጣ እያወጣ አብዛኞቹን ቤቶች የማያስረክብ ሲሆን፣ እነዚህን ቤቶች በገንዘብ እየቸበቹ ከፍተኛ ገንዘብ እያገኙባቸው ነው። የተሰሩ ቤቶችን እንኳን በጊዜው ለማስረከብ በጎን የተሸጡና ያልተሸጡ ቤቶችን ለመለየት አስቸጋሪ መሆኑንም ምንጮች ይገልጻሉ።