በሐዋይ የእሳተ ጎመራ ፍንዳታ ተቀሰቀሰ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 26/2010)  በሐዋይ የእሳተ ጎመራ ፍንዳታ ተቀሰቀሰ።

የኪላዊያ እሳተ ጎሞራ ፍንዳታን ተከትሎም 2 ሺ የሚጠጉ ሰዎች በአስቸኳይ ከቀያቸው እንዲነሱ ተደርገዋል።

ትልቅ ስፋት አለው በተባለው ደሴት የተከሰተው እሳተ ጎመራ ፍንጣቂ ወደ ዛፎችና መንገዶች ላይ መወርወር መጀመሩ ደግሞ አደጋውን የከፋ አድርጎታል ተብሏል።

የኪላዊያ እሳተ ጎመራ በአለም ላይ ከሚገኙትና በማንኛውም ሰአት ሊፈነዱ ይችላሉ ተብለው ከሚጠበቁት እሳተ ጎመራዎች አንዱ ነው።

ዛሬ ላይ በሃዋይ መፈንዳቱ የተነገረው ይሄ እሳተ ጎመራ እስካሁን 1700 ሰዎችን ከቀያቸው አፈናቅሏል።

እሳተ ጎመራው እስከ 10 ሺ የሚጠጉ ነዋሪዎችንም ከቀያቸው ሊያፈናቅል ይችላል ብሏል ቢቢሲ በዘገባው።

እሳተ ጎሞራውን ተከትሎ ተደጋጋሚ  ርዕደ መሬት መከሰቱም ታውቋል።

እስካሁን ግን አደጋውን ተከትሎ በሰው ሕይወት ላይ ስለደረሰው ጉዳት የተባለ ነገር የለም።

በግዛቲቱ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ መታወጁንና ነዋሪዎችን ከቀያቸው የማሸሹ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብሏል ቢቢሲ   በዘገባው።

የከተማዋ አስተዳደር እንደገለጸው  ከእሳተ ጎመራው የሚወጣው ሰልፈሪክ ዳይ ኦክሳይድ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል የሚል ስጋትንም አጭሯል።

መንገዶች መሰነጣጠቃቸውንና ከእሳተ ጎሞራው የሚወጣውም እሳት ወደ አካባቢው ሊዛመት እንደሚችል እየተነገረ ነው።