(ኢሳት ዜና –ነሐሴ 4/2009 ሰሞኑን) በሌብነት ተጠርጥረው ወደ እስር ቤት ከተጋዙት የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ነጋዴዎችና ደላሎች ውስጥ 45ቱ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ለመመልከት ቀጠሮ የሰጠው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ ወደ ወህኒ ቤት እንዲመለሱ አድርጓል።
ባለፈው ሰኞ ፍርድ ቤት የቀረቡት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለማየሁ ጉንጆ በእስረኛ በተጨናነቀና መላወሻ በሌለው ክፍል ውስጥ መታሰራቸውን ለፍርድ ቤት ገልጸዋል።
ሰኞ ነሐሴ 1/2009 ከአቶ አለማየሁ ጉጆ ጋር ፍርድ ቤት የቀረቡት ባለፈው አርብ በተመሳሳይ በቁጥጥር ስር የዋሉት የመንገዶች ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤልና የስኳር ኮርፓሬሽን ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ኪሮስ ደስታ ናቸው።
ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ በሀገር ሀብት ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል የተጠየቁት አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል መረጃዎቹ ሲያገለግሉበት በነበረው ተቋም ውስጥ የሚገኝ መሆኑን በመግለጽ ድርጊቱን አልፈጸምኩም በማለት ለፍርድ ቤቱ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ስልጣናቸውን ከለቀቁና መንግስት ወደ ሌላ የሃላፊነት ቦታ ካዛወራቸው ሁለት አመታት እንደተቆጠሩም አስረድተዋል።
የስኳር ኮርፖሬሽኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ደስታም ድርጊቱን አልፈጸምኩም በማለት ቢከላከሉም ገና ከጣና በለስ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ የ135 ሚሊየን ብር ተጠያቂ መሆናቸው በፍርድ ቤቱ ተመልክቷል። እሳቸው ግን ስራዬን ከለቀኩ ሁለት አመት ሆኖኛል በማለት መከራከራቸውን ቀጥለዋል።
ባለፈው ሳምንት አርብ ያለመከሰስ መብታቸውን በፓርላማው ተገፈው ከፓርላማ ገና ሲወጡ ተይዘው ወደ እስር ቤት የተወሰዱት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አለማየሁ ጉጆ 20 ሰዎች በታሰሩበት ጠባብ ክፍል ውስጥ መታሰራቸውን ለፍርድ ቤቱ ከማሳወቃቸውም ባሻገር ከቤተሰብ መገናኘት አለመቻላቸውን እንዲሁም የስኳር በሽተኝነታቸውን ለፍርድ ቤቱ በማብራራት መፍትሄ ለማግኘት ጠይቀዋል።
በተያያዘ ዜና ቀደም ሲል የተያዙትና ዛሬ ፍርድ ቤት በመቅረብ ዋስትና የጠይቁት 45ቱ ተከሳሾች የዋስትና ጥያቄያቸውን ፍርድ ቤቱ ባለመቀበሉ ወደ እስር ቤት እንዲመለሱ ተደርጓል።