በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ላይ እተከሰተ ያለው ጉዳት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የቤተ ክርስቲያኗ አመራሮች አስታወቁ፡፡

ጥቅምት ፲፪(አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-በቅዱስ ላሊበላ ገዳም የሰው ሃይል አስተዳደር የሆኑት ቀኝ ጌታ በላይ አናውጥ ከልዩ ልዩ አካባቢ ለመጡ ጋዜጠኞችና ጎብኝዎች እንደ ገለጹት ገዳሙ በዝናብና ጸሃይ እየደረሰበት ያለው ጉዳት ቅርሶቹን በአስከፊ ደረጃ እያፈረሳቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቅርሶቹን ከጸሐይና ዝናብ ይከላከላል ተብሎ ከለጋሽ ሃገሮች በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተሰራው መጠለያም ምሰሶዎች ብረት የተተከሉት በቤተ መቅደሶቹ ላይ በመሆኑና የብረቱም ክብደት ከፍተኛ መሆን ስጋቱን ከፍ እንዳደረገባቸው የቤተ ክርስቲያኗ አባቶች ተናገረዋል፡፡ከዚህ ጋር በተያያዘም መጠለያዎቹ በየአምስት

አመታት ጥገና ይደረግላቸዋል ቢባልም ከስድስት አመት በላይ ሳይጠገኑ መቆየታቸው ሌላው አሳሳቢ ችግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መጠለያ የተሰራላቸው አብያተ ክርስቲያናት በተወሰነ ደረጃ ከዝናብና ከጸሀይ መጠበቅ እንደቻሉ ቢያምኑም አንዳንድ የመጠለያ ምሶሶዎች የቆሙበት ቦታ ቤተ ክርስቲያን ወይም የውስጥ ለውስጥ መንገድ ስላሉበት ተግባራዊ ሲሆን የዲዛይን ስህተት ተፈጽሟል ብለው ያምናሉ፡፡ ከቤተ አማኑኤል ወደ ቤተ ገብርኤል በሚወስደው የምድር ውስጥ የጨለማ መንገድ ላይ መጠለያውን የሚሸከም ከባድ ብረት መቆሙ፣ለቤተ ማርያም የተሰራው መጠለያ ምሰሶ የቆመበት ቦታም በስላሴ መቅደስ ጣሪያ ላይመቆሙ ለስጋታቸው እንደ ማሳያ ያቀርባሉ፡፡

ከዚህ ባሻገር መጠለያ የተሰራላቸውም ቢሆኑ ከፍተኛ የመሰንጠቅ አደጋው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ እንደሚገኝ በቤተ አማኑኤል ላይ የደረሰውን እንደ ማስረጃ ያቀርባሉ፡፡በተለይ ከአብያተ ክርስቲያናቱ መካከል ቤተ ገብርኤል ወሩፋኤል  በስፋት የመሰነጣጠቅ እና ዝናብ የውስጡን ግድግዳ በመፈረካከስ አደጋ ቢያደርስበትም ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ላይም መጠናቸው የማይተናነሱ ጉዳቶች እንዳሉባቸው ቀኝ ጌታ በላይ ተናግረዋል፡፡

የቅዱስ ላሊበላ ገዳም አስተዳዳሪ መምህር አባ ወልደትንሳዔ አባተ በበኩላቸው ለዓለም ድንቅ የሆኑት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለረዢም ጊዜ በዝናብና በጸሀይ የመሰንጠቅ አደጋ ቢከሰትባቸውም የጥገና ስራ ስላልተሰራላቸው ህልውናቸው አደጋ ውስጥ እንደገባ ይናገራሉ፡፡በዚህ በኩል በስላሴ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚገኙ የግድግዳ ላይ ቅርፃ ቅርፆች ማንነታቸው እየጠፋ መጥቷል የሚል ስጋትም አለባቸው፡፡  ጉዳዩን ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ የጥገና ጥያቄ ደብዳቤ ቢላክም ወደ ጥገና መግባት ባለመቻሉ ችግሩ እየተስፋፋ መጥቷል ብለዋል፡፡ለዚህ ማረጋገጫቸውም ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ  ቅርስ ጥናት ና ጥበቃ ባለስልጣናት የተጻፉ ሰባት ደብዳቤዎችን በዋቢነት አቅርበዋል፡፡እነዚህ ቅርሶች አስቸኳይ ጥገና የማይደረግላቸው ከሆነ ቅርስ ወዳዱን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያሳዝን አደጋ ተከስቶ የአለም ህዝቦች መነጋገሪያ እንዳንሆን በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የፌደራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ በቅርሶቹ ላይ ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን በማመን ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡ከአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ ቢገኝም በተለያዩ ውስጣዊ ችግሮች የተነሳ የጥገና ስራው እዲዘገይ አስገድዷል በማለትም ገልጸዋል፡፡

የመጠለያ ግንባታው ሲሰራ በኪነ ህንጻ አማካሪነት የሰሩት በአዲሰ አበባ ዩኒቨርስቲ ረዳት ፐሮፌሰር በመሆን የሚያገለግሉት ዶክተር መሰለ ሀይሌ የመጠለያው ምሰሶዎች የቆሙት በወጣላቸው ዲዛይን መሰረት ቢሆንም የመጠገኛ ጊዜያቸው ስላለፈባቸው መስተካከል እንደሚገባቸው ያምናሉ፡፡በጊዜ ብዛት የምሰሶዎቹ ብሎኖች ቢላሉ ሌላ አደጋ ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ፈጥኖ እየተከታተሉ ጥገና ማድረግ ያስፈልጋል የሚል አስተያት ሰጥተዋል፡፡

አሁንም ኪነህንፃው የመፈራረሱ አደጋ እንደተጋረጠበት ነው፡፡የቤተክርሰቲያኒቱ አባቶች መፍትሄ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ሰሚ አላገኘንም ይላሉ፡፡ለኪነ ህንጻው ማደሻ የተገኝውን ገንዘብ ለጥናት ዲዛይን በሚል ሰበብ እየባከነ ነው በማለት የቤተክርስቲያኒቱ አመራሮች ያማርራሉ፡፡