በሊባኖስ አንዲት መንገድ ላይ ተጥላ መገኘቷ ተሰማ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 25/2010) በሊባኖስ አንዲት ኢትዮጵያዊ ዛሬ በአሰሪዎቿ ክፉኛ ተደብድባ መንገድ ላይ ተጥላ መገኘቷ ተሰማ።

ልጅቷን መንገድ ላይ ተጥላ ያገኛት አንድ ኢትዮጵያዊም ወደ ሆስፒታል ወስዷት ሕክምናዋን በማግኘት ላይ እንደምትገኝ በምስል ተደግፎ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

አዊ ጉደታ የተባለችውና በሊባኖስ ጎዳና ላይ ተጥላ የተገኘችው ኢትዮጵያዊ የአምቦ አካባቢ ተወላጅ እንደሆነችና እድሜዋም ከሃያ አመት በታች እንደሆነም ታውቋል።

እናም ኢትዮጵያዊቷ ሳራ በተባለች አሰሪዋ ተደብድባ በቤሩት መንገድ ላይ ደሟን እየዘራች ባለችበት ወቅት መገኘቷንም ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ኢትዮጵያዊው ልጅቷን እንዳገኛትናም ወዲያውኑ የተባበሩት መንግስታት ቢሮ በመደውል አምቡላንስ ጠርቶ ወደ ሆስፒታል እንድትወሰድ ማድረጉም ታውቋል።

ኢትዮጵያዊቷ ለ10 ወራት ያህል በቤይሩት እንደኖረችና አሰሪዋም ደሞዟን ከፍላት እንደማታውቅም ተናግራለች።

በሊባኖስ ከሌሎች ሃገራት ለስራ ለሚመጡ ዜጎች የየሃገራቱ ኤምባሲዎች ለመብታቸው በመቆም ከብዝበዛና እንግልት ሲታደጓቸው ኢትዮጵያውያኑ ግን ለዚህ እድል አለመብቃታቸውን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀን ሁለት ጊዜ ወደ ሊባኖስ በረራ የሚያደርግ ሲሆን በየቀኑ ከሚገቡ መንገደኞች ውስጥ አብዛኞቹ ለስራ የሚገቡ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል።

አንድ በሊባኖስ የሚኖር ኢትዮጵያዊ እንደተናገረው በየቀኑ ሊባኖስ የሚገቡት ኢትዮጵያውያን አብዛኞቹ በለጋ እድሜ ላይ የሚገኙ ናቸው።

ነገር ግን ኢትዮጵያውያኑ ከሃገራቸው ይዘው የሚወጡት ፓስፖርት ግን የሚያሳየው ልጆቹ በ26ና በ27 አመት የእድሜ ክልል ውስጥ መሆናቸውን ነው።

ይህ ደግሞ እነሱን ስራ አስቀጥሮ ለሚገኝ የገንዘብ ጥቅም ሲባል እንደሚፈጸምም ተነግሯል።

ኢትዮጵያዊቷ አዊ ጉደታ በአሁኑ ወቅት ራፊክ ሃሪሪ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ውስጥ የሕክምና እርዳታ በማግኘት ላይ ትገኛለች።

በአረብ ሃገራት ለስራ በሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ላይ አሰሪዎቻቸው ድብደባና እንግልት አንዳንዴም ግድያ እንደሚፈጽሙ ሲዘገብ መቆየቱ ይታወሳል።