በለንድን ኦሎምፒክ የሴቶች 5000 ሺህ ሜትር የፍፃሜ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ የበላይነታቸውን አሳዩ

ነሀሴ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ጠያይሞቹ ንግስቶች ለንደን ላይ  አክሊላቸውን ደፉ።አረንጓዴው ጎርፍ በለንደን ኦሎምፒክ ስታዲየም ፈሰሰ። በሴቶች 5ሺህ ሜትር የ ኦሎምፒክ ውድድር ድንቅ  ታሪክ ተሠራ። 1 ኛ ኢትዮጵያ 3ኛ ኢትዮጵያ 5 ኛ ኢትዮጵያ።

የ2004 የ ኦሎምፒክ ሻምፒዮን የሆነችው ጀግናዋ መሰረት ደፋር እንደ ልማዷ በመጨረሻው መቶ ሜትር ላይ ፍጥነቷን በመጨመር እና የኢትዮጵያውያን ተቀናቃኝ የሆነችውን- ኬንያዊቷን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን ቪቪያን ቸሩዮትን  ከሁዋላ በማስከተል  የድሉን መስመር ቀድማ አቋርጣለች።

መሰረት ወድድሩን ያጠናቀቀችው በ 15 ደቂቃ 4 ነጥብ 25 ሰከንድ ነው።

ኬንያዊቷ ቪቪያን ቸሩዮት ርቀቱን  በ 15 ደቂቃ 04. 73 ሰከንድ በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያ ስታገኝ፤ በለንደን ኦሎምፒክ ለአገሯና ለራሷ የመጀመሪያውን ወርቅ ከቀናት በፊት ያስገኘችው የ 10 ፣000 ሜትር ንግስቷ ጥሩነሽ ዲባባ  በዚህም  ወድድር ሦስተኛ በማጠናቀቅ ተጨማሪ የነሐስ ሜዳሊያ አስገኝታለች።

በውድድሩ አጋማሽ ላይ በተቀናቃኞቿ ተጠልፋ ከመውደቅ ለጥቂት የተረፈችው ቆፍጣናዋ ገለቴ ቡርቃ ደግሞ ፤ ውድድሩን በ5ተኛነት አጠናቃለች።

ጥሩነሽ፤ከአራት ዓመት በፊት በቤጅንግ የተካሄደውን  የ5 ሺህ እና የ10 ሺህ ሜትር በአንደኝነት በማጠናቀቅ  በአንድ  ኦሎምፒክ ሁለት ወርቅ ማግኘቷ ይታወሳል።

 

ክትናንቱ ምሽት  የ5000 ሺህ ሜትር ፍፃሜ  በሁዋላ የዓለምን ትኩረት የሳበው ሌላው ትዕይንት፤ አንበሳዋ መሰረት ደፋር ካሸነፈች  በሁዋላ ደስታዋን የገለጸችበት መንገድ ነው።

መሰረት ውድድሩን በአንደኝነት እንዳጠናቀቀች ወዲያውኑ በአንገቷ ውስጥ እጆቿን በመስደድ፤ በውስጥ ደብቃ ይዛው የነበረውን እና ድንግል ማሪያም ህፃኑን ኢየሱስን አቅፋ የሚያሳየውን ምስል በማውጣት  አሰፍስፈው ሊቀርጿት ለሚጠባበቁት ጋዜጠኞች በማሳየት  ነው ደስታዋንና የውስጥ ስሜቷን  ስትገልጽ የታየችው።

ሲ.ኤን ኤ የተባለ የዜና አገልግሎት ተቋም ፦” ድንግል ማርያም  ከኦሎምፒክ የወርቅ ሯጯ ጋር በመሆን  ውድድሩን አሸነፈች” በማለት ነው ሁኔታውን የገለፀው።

ዓለምን ያስገረመው እና ያስደነቀው የመሰረት  የትናንት ምሽት ትዕይንት ግን ይህ ብቻ አይደለም። ለአሸኛፊዎች ወደተዘጋጀው ሥፍራ ወጥታ የወርቅ ሜዳሊያ ከተጠለቀላት በሁዋላ  በነበረው የሰንደቅ ዓለማ ስነ-ስርዓት ፤ከንፈሮቿ እየተንቀጠቀጡ  በእንባ ጎርፍ ስትታጠብ  ታይታለች።

ይህ አሳዛኝ ትዕይንትም  የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ልብ እንደነካ በፌስ ቡክ፣በትዊተር እና በሌሎች ማህበራዊ መገናኛዎች የሚሰጡ አስተያየቶችና የሚፃፌ የመወድስ ግጥሞች ያመለክታሉ።

“ለመሰረት እና ለጥሩዬ ማስታወሻ” ይሁን በማለት በፌስ ቡክ ከተለቀቁት በርካታ ግጥሞች መካከል፦

“በአለም አደባባይ- ባንዲራዬን ሳየዉ፣

ከንፈሮቼን ሳይቀር የሚያንዘረዝረዉ፣

የወርቅ እኮ አይደለም – የሀገሬ ፍቅር ነዉ’የሚል ይገኝበታል።

ከዚያ በማስከተል በተካሄደው የ 1500 ሜትር የሴቶች የፍፃሜ ውድድር  በሮም የጎልደን ሊግ አሸናፊዋ  በፈጣኗ አበባ አረጋዊ የተወከለችው ኢትዮጵያ ተጨማሪ ወርቅ እንደምታገኝ በስፋት የተጠበቀ ቢሆንም፤ በታክቲክ ስህተት ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል።

በለንደን ኦሎምፒክ የደረጃ ሰንጠረዥ  ኢትዮጵያ በ 3 ወርቅ እና በሶስት ነሐስ፤ ከ ዓለም በ22ኛ ከአፍሪካ ደግሞ በ 2ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

የኢትዮጵያ የቅርብ ተቀናቃኝ የሆነችው ኬንያ ደግሞ በሁለት ወርቅ፤ ሁለት ብር እና በሦስት ነሀስ የ 26 ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ከአፍሪካ አንደኛ እየመራች ያለችው በዓለም የደረጃ ሰንጠረዥ ከ ኢትዮጵያ አንድ ደረጃ ከፍ ብላ  በ 21 ኛ ደረጃ የተቀመጠችው ደቡብ አፍሪካ ነች።

ደቡብ አፍሪካ እና ኢትዮጵያ እኩል ሦስት፣ ሦስት ወርቅ ያላቸው ሲሆን፤ በነሀስ ሜዳሊያም ኢትዮጵያ 3 ለ 1 ትመራለች።  ደቡብ አፍሪካ ከኢትዮጵያ ከፍ ብላ የተቀመጠችው አንድ ተጨማሪ የብር ሜዳሊያ ስላላት ነው።

በመሆኑም በቀጣይ በሚደረጉ የወንዶች  5000 ሺህ ሜትር  ፍፃሜ እና የማራቶን ወድድሮች ኢትዮጵያ ተጨማሪ የወርቅ አለያም የብር ሜዳሊያ በማግኘት ከደቡብ አፍሪካና ከኬንያ  የተሻለ ውጤት ካስመዘገበች፤ የለንደኑን ኦሎምፒክ ከ አፍሪካ አንደኛ ሆና ለማጠናቀቅ ትችላለች።

____________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide