በሆሳዕና ከተማ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ። ባህር ዳር የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት በ3 አቅጣጫዎች ሊገቡ የነበሩ ቦንቦች ተይዘዋል። በሃረር ከተማ ደግሞ የድጋፍ ሰልፍ እንዳይካሄድ ክልከላ ተደርጓል።

በሆሳዕና ከተማ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ።
ባህር ዳር የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት በ3 አቅጣጫዎች ሊገቡ የነበሩ ቦንቦች ተይዘዋል። በሃረር ከተማ ደግሞ የድጋፍ ሰልፍ እንዳይካሄድ ክልከላ ተደርጓል።
(ኢሳት ዜና ሰኔ 20 ቀን 2010 ዓ/ም) ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የጀመሩትን የለውጥ እንቅስቃሴዎች በመደገፍ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ዛሬም በሆሳና ከተማ ቀጥሎ ውሎአል።
የከተማዋ ነዋሪዎች በሆሳና ስታዲየም በነቂስ በመውጣት ለጠቅላይ ሚንስትሩ ያላቸውን አጋርነት በመግለጽ ሰሞኑን በክልሉ የተከሰቱትን በማንነት ላይ ያነጣጥሩ ጥቃቶችን አውግዘዋል። ደኢህዴን ራሱን ከህወሃት ተጽዕኖ እንዲያላቅቅ ሰልፈኞች ጥሪ አቅርበዋል። “ባንተባበር ተበልተን ነበር ፣ አብይ ሲመጣ ወኔያችን መጣ” የሚሉ መልዕክቶችም በጭፈራ ተስተጋብተዋል።
በተመሳሳይ ዜና የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድን የለውጥ ጎዳና ለመደገፍ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች የጠሩት የድጋፍ ሰልፍ በመስተዳደሩ እውቅና አግኝቷል። እሁድ ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ.ም የሚደረገውን የድጋፍ ሰልፍ በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን የከተማዋ ወጣቶች የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረጉ ይገኛሉ። ወጣቶቹ ከተማዋን በሰንደቅ ዓላማዎች በማስዋብ የኢትዮጵያን ባንዲራ ለብሰው ለሰላማዊ ሰልፉ ከወዲሁ ዕውቅናና ድምቀት እየሰጡት ነው። አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ሪቫኖች እንዲሁም ባንዲራዎችን በመሸጥ ላይ የተሰማሩ ወጣቶችም ስራ በዝቶባቸዋል።
የእሁዱን ሰልፍ በማደናቀፍ በህዝቡ ላይ አደጋ ለማድረስ በማቀድ ከከተማዋ ሦስት አቅጣጫዎች ሊገቡ የነበሩ ቦንቦችን መያዙን የከተማው ፖሊስ አስታውቋል። ሕዝቡ እራሱንና አገሩን እንዲጠብቅ ተጠርጣሪዎችን አስቀድሞ ለጸጥታ አካላት በማሳወቅ ሰላሙን እንዲያረጋግጥ ሲል ፖሊስ ጥሪ ቀርቧል።
የሃረር ከተማ ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድን በመደገፍ ቅዳሜ ሰኔ 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጠርተውት የነበረው የድጋፍ ሰልፍ እንዳይካሄድ ተከልክሏል። ክልከላው የተካሄደው በክልሉ በከፍተኛ ሁኔታ ታጥቆ የሚገኙት ወታደሮች ይህን ምክንያት በማድረግ የእርስ በርስ ግጭት እንዲነሳ ሊያደርጉ ይችላሉ በሚል ፍርሃት ነው።