ኢሳት (ጥር 09 ፥ 2008)
በሆሳዕና ከተማ ከመንጃ ፈቃድ ቅጣት እና አስተዳደር ብልሹነት ጋር በተያያዘ የህዝብ የትራስፖርት ማመላለሻ አገልግሎት ለሁለት ቀን ተቋርጦ መዋሉት ዛሬ ሰኞ ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመለከተ።
አንድ ሆሳዕና ወደሌላ ወረዳ ወይም ከወደ ዋና ዋና ከተሞች የሚያጓጉዙ የትራንስፖት መገናኛ አገልግሎቶች በመቋረጣቸው ህዝቡ ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ውስጥ ላይ እንደሆነ አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ በሆሳዕና የሚኖሩ ሰው ለኢሳት በስልክ ተናግረዋል።
“መንግስት ያወጣው አዲሱ ህግ አንድ ሹፌር 3 ጊዜ አንድ አንድ ሺ ብር ከተቀጣ መንጃ ፈቃዱን ይነጠቃል የሚለው ነው አድማውን ያስነሳው” ያሉት አንድ አስተያየት ሰጪ፣ አድማውን ተላልፎ ከቡታጅራ ሆሳዕና ይጓዝ የነበረ አንድ ሃይሩፍ የትራስፖርት ተሽከርካሪም ወራቤ ላይ በትራንስፖርት አገልግሎት ሰራተኞች እና በህዝቡ እንደወደመ ተነግሯል።
አዲሱን የመንግስት መመሪያ በመቃወም የሆሳዕና፣ ጉራጌ እና ወላይታ ዞኖች ባሉት ከተሞች የሚኖሩ ነዋሪዎች በአድማው መሳተፋቸው ታውቋል።
የአካባቢው ህብረተሰብም ታምቀው የቆዩ የመልካም አስተደደር ችግሮችን እየገለጸ ያለበት አጋጣሚ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት አስታውቀዋል።
ትናንት እሁድና ዛሬ ሰኞ ከባጃጅ ጀምሮ ሁሉም የትራስፖርት አገልግሎቶች በመቋረጣቸው፣ ከከተማዋ የሚወጣም ሆነ የሚገባ ምንም አይነት የትራስፖርት አገልግሎት ተሽከርካሪ እንደሌለ ታውቋል።
ከአድማው ጋር በተያያዘ በሃድያ ዞን ማረሚያ ቤት 4 ሰዎች በመንግስት ሃይሎች መታሰራቸው ተነግሯል።
የመንግስት አዲሱን አሰራር በመቃወም ነገ ማክሰኞ በሆሳዕና ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ እንደተጠራ በአካባቢው የሚኖሩ ሰው ለኢሳት ተናግረዋል።