የካቲት 2 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጡት በከተማው በተከሰተው የውሀ እጥረት የተነሳ የአካባቢው ህዝብ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቋል።
ውሀ ከጠፋ ወራት ማስቆጠራቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች በተለይ ባለፈው ሳምንት መብራት እና ውሀ በአንድ ላይ በመጥፋቱ የህዝቡን ችግር አባብሶታል።
ህዝቡ የወንዝ ውሀ ለማግኘት 8 ኪሎሜትር ድረስ መጓዝ ግድ እንደሆነበት ነዋሪዎች ይናገራሉ። 20 ሊትር የወንዝ ውሀ በ10 ብር ለመግዛት መገደዳቸውንም ያክላሉ የውሀ መጥፋት ሳያንስ በየጊዜው የሚታየው የኑሮ ውድነት ህይወታቸውን መሪር እንዳደረገባቸውም ነዋሪዎች አክለው ተናግረዋል።
አቶ መለስ ዜናዊ ሰሞኑን የገንዘብ ግሽበት ከ40 በመቶ ወደ 32 በመቶ ዝቅ ማለቱን ለፓርላማ አባላት ቢናገሩም፣ ህዝቡ ግን የሚቀበለው አልሆነም። አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የመንግስት ሰራተኛ “እርሳቸው 3 በመቶ ደረሰ ቢሉ እንኳ የሚያምናቸው ሰው ይኖራል ብለህ ታስባለህ? እኛ ኑሮው ሲወጣ እንጅ ሲወርድ አይተን አናውቅም ሲል” ተናግሯል።
በመንግስት ደጋፊነቱ ስሙ የሚነሳው ሪፖርተር ጋዜጣም ባወጣው ርእሰ አንቀጽ ‹‹ወጣ ወጣና እንደ ሸንበቆ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ›› የሚለውን ተረት እያስታወስን፣ የኑሮ ውድነቱ እንደ ሸንበቆ በየቀኑ ወደላይ ቢወጣም አንድ ቀን ይወርዳል፤ እንደ ሙቀጫም ይንከባለላል ብለን ጠብቀን ነበር፡፡
እንደ ተረቱ ግን አልሆን አለ፡፡ የኑሮ ውድነት እንደ ሸንበቆ ወጣ ወጣ እንጂ እንደ ሙቀጫ አልንከባለል ብሏል፡፡
ኑሮ እየከበደ ነው፡፡ በዝቅተኛና በመካከለኛ ደረጃ ያለውም የኅብረተሰባችን ክፍል ለዕለታዊ ኑሮ የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ነገር ለመግዛት አቅም ባጣበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን” ካለ በሁሏ ” እንዴት ነው ነገሩ; ሁሉም ነገር እየጨመረ ነው፡፡ እውነት ሁሉም ጭማሪ ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዘ ነውን? እውነት ግሽበት ያስከተለው ነውን? እውነት ከነዳጅ ዋጋ የተያያዘ ነውን? ስግብግብነት ያስከተለው ነው ተብሎስ የሚታለፍ ነውን? ዋናው መንግሥትን፣ ሌላ የሚመለከተው አካል ካለም እሱን፣ ኢኮኖሚስቶች የሚነገሩን ከሆነ ደግሞ እነሱን የምንጠይቀው ጥያቄ ግልጽ ነው፡፡ የአቅርቦቶች ዋጋ በየቀኑ መናር ዋናውና ትክክለኛ ምክንያቱ ምንድን ነው? ኑሮ መወደዱ ብቻ ሳይሆን ምክንያቱ በግልጽ በሚመለከተው አካል በየሁኔታው አለመነገሩና ሕዝቡ እንዲያውቀው አለመደረጉ ራሱን የቻለ ሌላ ችግር እየሆነ ነው፡፡ ወቅታዊውና እውነተኛው ምክንያት ይነገረን፡፡ መፍትሔውስ? ለኑሮ ውድነቱ በየቀኑ መናር መፍትሔው ምንድነው; አንድ ቀን ይወርድ ይሆናል እያሉ ብቻ በተስፋ መጠበቅ? በቂ የአገር ውስጥ ምርት ባይኖርም ለሞራል ‹‹በአገሬ ምርት እኮራለሁ›› እያሉ መዘመር; ወይስ በተጨባጭ መፍትሔ ሊሆን የሚችል ዕርምጃ ይኖራል;?” በማለት ጥያቄ አዘል ሀታተውን አስፍሯል።
በቅርቡ መምህራን የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ባለመቻላቸው መንግስት ያቋቋመው ተለጣፊው የመምህራን ማህበር የደሞዝ ጭማሪ መጠየቁ ይታወሳል። ማህበሩ ጥያቄያችን በአፋጣኝ ካልተመለሰ የስራ ማቆም አድማ እንጠራለን ብሎ በመዛቱ የመንግስት ባለስልጣናት መበሳጨታቸው መዘገቡ ይታወሳል።