በሆለታ ከተማ ከገበሬዎች ለወሰደው የአበባ እርሻ መሬት ኪራይ ክፍያ ያልፈጸመ የህንድ ኩባንያ መሬቱን እንዲያስረክብ ተወሰነ

ኢሳት (ሚያዚያ 18 ፥ 2009)

የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤት በሆለታ ከተማ ከገበሬዎች ለወሰደው የአበባ እርሻ መሬት መክፈል የሚጠበቅበትን የኪራይ ክፍያ ያልፈጸመ አንድ የህንድ ኩባንያ መሬቱን እንዲያስረክብ ወሰነ።

ፍርድ ቤቱ በቅርቡ የሰጠውን ይህንኑ ውሳኔ ተከትሎ ኢትዮጵያን ሚዶውስ የተሰኘው ኩባንያ ከ13 አርሶ አደሮች በኪራይ የወሰደውን 108 ሄክታር መሬት መመለሱን በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ይሁንና የኩባንያውን ባለድርሻዎች ከሁለት አመት በፊት ጀምሮ ለአርሶ አደሮቹ መክፈል የነበረባቸውን ኪራይ ሳይከፍሉ ከሃገር መኮብለላቸው ተመልክቷል።

የህንዱ ካራቱሪ እህት ኩባንያ የሆነው ይኸው የአበባ አምራች ድርጅት በአካባቢው ለረጅም አመታት ሲሰራ የቆየ ሲሆን፣ በኪራይ የወሰዳቸውን መሬት በአግባቡ ካለመጠቀሙ በተጨማሪ ለአርሶ አደሮች መክፈል የነበረበትን የመሬት ኪራይ ሳይከፍል መቆየቱን የክልሉ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

በጋምቤላ ክልል ሰፋፊ የእርሻ መሬትን ተረክቦ የነበረው ካራቱሪ ኩባንያ በገባው ቃል መሰረት የኢንቨስትመንት ስራን አላከናወነም ተብሎ ፈቃዱ ባለፈው አመት መሰረዙ ይታወሳል። ይኸው ኩባንያ ስራውን ለመጀመር ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሚሊዮን ብር የሚቆጠር ብድር ቢወስድም፣ የወሰደውን ብድር እንኳን መመለስ አለመቻሉ ሲገልፅ ቆይቷል።

ኩባንያው በተለያዩ ጊዚያቶች ከ100 ሺ በላይ ሄክታር መሬት ለልማት ቢረከብም የእርሻ ስራውን ማከናወን የቻለው ግን ከ20 በመቶ በታች መሆኑም ተመልክቷል።

የዚህ እህት ኩባንያ በሆለታ ከተማ ምን ያህል የኪራይ ገንዘብ ሳይከፍል መቅረቱን የኦሮሚያ ክልል ሃላፊዎች የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።

ባለፈው አመት በክልሉ ተቀስቅሶ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ወቅት በርካታ አርሶ አደሮች ለተወሰደባቸው የእርሻ መሬት በቂ ካሳ እንዳልተሰጣቸው ተቃውሞ ሲያሰሙ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ ሚዶውስ የተሰኘው የህንዱ ኩባንያ ከ 131 አርሶ አደሮቹ መሬትን በምን ያህል ክፍያ ተከራይቶ እንደቆየም የታወቀ ነገር የለም።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በጋምቤላ ክልል ባለሃብቶች ሲሰጥ የቆየው ሰፋፊ የእርሻ መሬት በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ኪሳራ እንደደረሰበት ሲገልፅ ቆይቷል።

ቁጥራቸው ያልታወቀ የህንድ ባለሃብቶች ከባንኩ የወሰዱትን ብድር ሳይመልሱ ከሃገር መውጣታቸውም ተገልጿል።

መንግስት በበኩሉ የህንድ ባለሃብቶች የወሰዱትን እንዲመልሱ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ በቅርቡ አስታውቋል።