ኢሳት (ጥር 2 ፥ 2009)
በህገወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል የተጠረጠረ የአንድ ኢትዮጵያዊ የፍርድ ሂደት በማልታ መታየት መጀመሩን የሃገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።
ሰኞ በሃገሪቱ በሚገኝ አንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩ መታየት የጀመረው የ58 አመቱ ሃዱሽ አባይ ከ11 አመት በፊት 181 አፍሪካዊ ስደተኞችን ወደ ማልታ በተደራጀ የህገወጥ ድርጊት ማጓጓዙን በግለሰቡ ላይ የተመሰረተ ክስ አመልክቷል።
አቶ ሃዲሽ በጉዳዩ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2006 አም የዋስትና መብቱ ተጠብቆለት ከእስር ቤት እንዲወጣ ቢደረግም ከሃገሪቱ ኮብልሎ መቆየቱን ማልተስ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
ግለሰቡ ከሃገሪቱ በማምለጡ ምክንያት የፍርድ ሂደቱ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፣ የስዊዘርላንድ የጸጥታ ሃይሎች ተፍላጊውን አቶ ሃዱሽን ባለፈው ግንቦት ወር በቁጥጥር ስር አውለው ለሃገሪቱ መስጠታች ታውቋል።
የማልታ ባለስልጣናትም ከስደተኞቹ መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብ ሰብስቧል የተባለው የሃዲሽ ዳግም የክስ ሂደት ሰኞ በይፋ መጀመሩንና ዘጠኝ ዳኞች በጉዳዩ ላይ ፍርድን ለመስጠት የተለያዩ የክስ መረጃዎችን መመልከት እንደጀመሩ የቴሌቪዥን ጣቢያው አመልክቷል።
የማልታ ከሳሽ አቃቤ ህግ ተጠርጣሪው ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር 181 ዱን ስደተኞች ከሊቢያ ወደ ማልታ ማጓጓዙን በክሳቸው አቅርበዋል።
ይኸው ተጠርጣሪ ስደተኞቹ ማልታ ከገቡ በኋላ ጉዞአቸውን ወደ ጣሊያን የሚቀጥሉበትን ሁኔታዎችና ክፍያዎችን የተመለከቱ ጉዳዮች ለማስፈጸም በማልታ ይንቀሳቀስ እንደነበር የቀረበበት ክስ ያስረዳል።
የ58 አመቱ ሃዱሽ አባዩ በቀረቡበት የተለያዩ ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የረጅም አመት የእስር እና የገንዘብ ቅጣት ይጣልበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በአውሮፓ የምትገኘው ማልታ ከጣሊያኗ የሲሲሊ ደሴት በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ ካላት አቀማመጥ አመቺነት በርካታ ስደተኞች በሰሜናዊ አፍሪካ በኩል እንደሚጓጓዙባት ይታወቃል።
ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት ስደተኞች ከሊቢያ በመነሳት በማልታ በኩል ወደ አውሮፓ ለመግባት ጥረት እንደሚያደርጉም መረጃዎች የመለክታሉ።