ኢሳት (ግንቦት 9 ፥ 2008)
መንግስት ወደተባበሩት አረብ ኤመሬት የሚደረግ የሰራተኞች ጉዞ እንዲቋረጥ ቢያደርግም በየዕለቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ተለያዩ የአረብ ሃገራት በህገ-ወጥ መንገድ በመጓዝ ላይ መሆናቸው ተገለጠ።
ባለፈው አንድ አመት ብቻ በተመሳሳይ ሁኔታ የተጓዙና የተለያዩ ችግሮች ያጋጠሟቸው 5ሺ ኢትዮጵያውያን በቅርቡ ወደሃገራቸው እንዲመለሱ መደረጉንም ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ከሃገር በመውጣት ላይ ያሉ ሰዎችን መቆጣጠር እንዳልተቻለና በርካታቹ ህጋዊ የጉብኝት ቪዛን እየያዙ በመውጣት ላይ መሆናቸውን ገልጿል።
የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ መገናኛ ብዙሃን በየዕለቱ በትንሹ 500 ኢትዮጵያውያን በተለያዩ አየር መንገዶች በመጠቀም ወደ ሃገሪቱ በመግባት ላይ መሆናቸውን በቅርቡ መዘገባቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያውያኑ ህገወጥ ጉዞ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የተናገሩት የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው፣ በጉብኝትም ይሁን በቤት ሰራተኝነት ቪዛ ስም ወደ ዱባይ የሚደረገውን ጉዞ ማስቀረት አይቻልም ሲሉ ምላሽን ሰጥተዋል።
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ግርማ ሸለመ አዲስ ህግ ተግባራዊ መደረግ ሲጀምር ሚኒስትሩ ህጋዊ የስራ ውል ፈርመው እንዲሄዱ ማድረግ ብቻ ነው የመስሪያ ቤቱ ስልጣን ሲሉ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
ህውገወጥ ጉዞዎን መቆጣጠር ባለመቻሉ ምክንያት በአሁኑ ወቅት በርካታ ኢትዮጵያውያን በዱባይና በሌሎች ጎረቤት ሃገራት ለችግር ተዳርገው እንደሚገኙም ታውቋል።
ነዋሪነታቸው በዱባይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው መመለሻ ትኬት ሳይዙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከሃገር ኣንዲወጡ የሚደረግበት አሰራር መፈተሽ እንዳለበት ለገልፍ ኒውስ ጋዜጣ በቅርቡ መግለጻቸውም ይታወሳል።