ኢሳት (የካቲት 23 ፥ 2009)
በህገወጥ መንገድ ወደ ሞዛምቢክ ገብተዋል የተባሉ 36 ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሃገሪቱ የኢሚግሬሽን መምሪያ አስታወቀ።
ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ በሞዛምቢክ ሰሜናዊ ግዛት በሆነው የናምፑላ አስተዳደር በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ እንዳሉ በሰው ጥቆማ ሊያዙ መቻላቸውን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። የግዛቲቱ ፖሊስ አዛዥ የሆኑት ዘካሪያስ ናኩቴ የኢሚግሬሽን የጸጥታ አባላትና የግዛቲቱ ፖሊስ በጋራ በመኖሪያ ቤቱ ላይ ባካሄዱት ከበባ ኢትዮጵያውያኑ በሰላም በቁጥጥር ስር ሊውሉ መቻላቸውን ለሞዛምቢክ ዜና አገልግሎት አስረድተዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያውያን በስደተኞች ያለ ምንም ህጋዊ ሰነድ በሞዛምቢክ ሊገኙ በመቻላቸው ወደ ሃገራቸው እንደሚመለሱ ሃላፊው አክለው ገልጸዋል።
የስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ መዳረሻ ያልታወቀ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት የተለያዩ የአህጉሪቱ ሃገራትን ለመሸጋገሪያነት እንደሚጠቀሙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የአለም አቀፉ ስደተኛ ድርጅት (IOM) ከኢትዮጵያ በመሰደድ ላይ ያሉ ሰዎች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጨመረ መምጣቱን በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2016 አም ብቻ ወደ 90ሺ አካባቢ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ጦርነት እልባት ወዳላገኘባት የመን መሰደዳቸውን የድርጅቱ መረጃ ያመለክታል።
ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ስደተኛም በጎረቤት ሱዳን፣ ሶማሊላንድ፣ እና ኬንያ በኩል ወደ ተለያዩ ሃገራት ለመሰደድ ጥረት እንደሚያደርጉ ታውቋል።
ባለፈው አመት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት በጉዞ ላይ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በማላዊ፣ ታንዛኒያ፣ ዚምባብዌ እንዲሁም በናሚቢያ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ሲዘገብ ቆይቷል።
የአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ስደተኞቹ ያለፍላጎታቸው ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ መደረጉ አለም አቀፍ ህጎችን የጣሰ ተግባር ነው በማለት ድርጊቱን እየተቃወሙት ይገኛል።