ኢሳት (ግንቦት 1 ፥ 2009)
የሞዛምቢክ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ወደ ሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ገብተዋል የተባሉ 24 ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ማክሰኞ አስታወቁ።
ለቀናት ያህል በሃገሪቱ ፖሊስ በቁጥጥር ስር የነበሩት ኢትዮጵያውያን ከአዲስ አበባ ሲነሱ የተሳሳተ ቪዛን ይዘው እንደተጓዙ የሞዛምቢክ የጸጥታ ሃላፊዎችን ዋቢ በማድረግ ዴይሊ ኔሽን የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል። ባለፈው ወር በተመሳሳይ መልኩ ወደ ሃገሪቱ ገብተዋል የተባሉ 13 ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ መደረጉ ይታወሳል።
በተለያዩ ጊዜያት ወደ ደቡባዊ አፍሪካ ሃገራት የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በመጨመር ላይ ሲሆን፣ ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ መዳረሻቸውን ደቡብ አፍሪካ ለማድረግ እቅድ እንዳላቸው ይነገራል።
በሞዛምቢክ በተደጋጋሚ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ በማላዊ ታንዛኒያ እና ጎረቤት ሃገራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በእስር ላይ እንደሚገኙም የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት (IOM) መረጃ ያመለክታል።
ከቀናት በፊት ከሞዛምቢክ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ከተደረጉት ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የባንግላዴሽ ዜጎች የተሳሳተ ቪዛን ይዘዋል ተብለው ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ በዘገባው አስነብቧል።
የሞዛምቢክ ባለስልጣናት ኢትዮጵያውያኑ ከአዲስ አበባ ሃስተኛ ቪዛን ይዘው መጥተዋል ቢባሉም፣ ቪዛውን ከየት እንዳገኙት ግን የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።
ከአንድ አመት በፊት በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነ ኢትዮጵያውያን ወደ ተለያዩ ሃገራት በመሰደድ ላይ መሆናቸውን የአለም አቀፉ ስደተኖች ድርጅት አመልክቷል።