(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 21/2010)በህገወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ የሚወጣው የአሜሪካን ዶላር እየተባባሰ መሆኑ ተገለጸ።
በተለይ የብር የውጭ ምንዛሪ ዋጋ በ15 በመቶ እንዲቀንስ ከተደረገ በኋላ ወደ ውጭ በህገወጥ መንገድ የሚወጣው ገንዘብና ገንዘቡን ለማውጣት የሚሞክሩ ግለሰቦች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ታውቋል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም ከኢትዮጵያ በህገወጥ መንገድ የሚወጣው ገንዘብ በአመት ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ መድረሱን አረጋግጠዋል።
የብር የውጭ ምንዛሪ ዋጋ በ15 በመቶ እንዲቀንስ ከተደረገ በኋላ ወደ ውጭ በህገወጥ መንገድ የሚወጣው ገንዘብና ገንዘቡን ለማውጣት የሚሞክሩ ግለሰቦች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መሄዱን የአዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ የመንገደኞች ጓዝ ጉዳይ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ በየነ ገልጸዋል።
ምክትል ስራ አስኪያጁ የገዥው ፓርቲ ንብረት በሆነው ሬዲዮ ፋና እንደገለጹት ባለፉት 15 ቀናት ውስጥ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ግለሰቦች አኳያ ሲታይ ገንዘብን በህገወጥ መንገድ የማስወጣት ድርጊት በተጠናና በተደራጀ መንገድ ሆን ተብሎ የሚከናወን ተግባር ነው ።
አቶ ሙሉጌታ አክለው እንደገለጹት በአውሮፕላን ማረፊያው በኩል ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ማዕድናትም ወደ ውጭ ሀገር በህገ ወጥ መንገድ እየወጡ ያሉበት ሁኔታ እየጨመረ ሄዷል።
ኢሳት በጉዳዩ ላይ ያናገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ እንደገለጹት ከኢትዮጵያ በህገወጥ መንገድ የሚወጣው ገንዘብ በአመት ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ደርሷል።
ይህ ደግሞ ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና ከአፍሪካ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ሀገራት ተርታ መሰለፋችንን የሚያመላክት ነው ብለዋል።
አንድ ሀገር ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ስትገባና በህዝብ ተቃውሞ ስትናጥ ከሚታዩ ምልክቶች ቀዳሚው በባለስልጣናትና ከመንግስት ጋር ትስስር ባላቸው አካላት ከሀገር ውስጥ ወደ ውጪ የሚያሸሽ የገንዘብ መጠን መጨመር እንደሆነ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ ማሳያ ሊሆን ይችላልም ሲሉ ባለሙያው ያክላሉ።
ከውጭ በሚመጡ የፍጆታ ምርቶች፣የጥሬ እቃና የማምረቻ ማሳሪያዎች ግዥ ምክንያት እንዲሁም የብር የመግዛት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ባሽቆለቆለበት ሁኔታ በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ወደ ውጭ መሸሹ በፍጆታ ምርቶች ላይ የሚታየውን ዋጋ እንደሚያንረውና የኑሮ ውድነቱን የባሰ ከቁጥጥር ውጪ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።