ነኅሴ ፳፩ (ሀያ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ነባር አመራሮቹ በመመረጥና በመምረጥ መብት በድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ የፈቀደው ህወሃት፣ ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በሁዋላ በስራ አስፈጻሚነት ሲያገለግሉ የነበሩ አብዛኞቹን መሪዎችን በድጋሜ መርጧል። አቶ አባይ ወልዱ የድርጅቱም የግንባሩም ሊቀመንበር ሆነው ሲመረጡ፣ ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ደግሞ ምክትል ሆነው ተመርጠዋል። ቀድም ብሎ ህወሃትን ሊለቁ ነው በሚል ሲወራባቸው የቆዩት ወ/ሮ አዜብ መስፍን በስራ አስፈጻሚነት ተመርጠዋል። ዶ/ር አርከበ እቁባይ፣ አቶ ስዩም መስፍንና አቶ ስብሃት ነጋ በማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት ሳይመረጡ ቀርተዋል።
አቶ አባይ ወልዱ በክልሉ የሚኖሩ ታማኝ ደጋፊዎቻቸውን በጉባኤ እንዲሳተፉ በማድረግ፣ እርሳቸው እና በእርሳቸው ዙሪያ ያሉት እንዲመረጡ አድርገዋል በሚል እርሳቸው እንዳይመረጡ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ የህወሃት አባላት እየተናገሩ ነው።
ምንም እንኳ አቶ አርከበ በጉባኤው ሲሰጡት ከነበረው አስተያየት በመነሳት እና ቀድም ብሎ በመተካካት ስም ከለቀቁት ጉባኤ እንደገና እንዲመለሱ ከመደረጉ አንጻር ፣ ወደ ህወሃት ከፍተኛ የአመራር ቦታ ሊመጡ ይችላሉ የሚል አስተያየት ሲቀርብ ቢቆይም፣ አቶ አርከበ ለማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት ሳይጠቆሙ ቀርተዋል። በዚህ ጉባኤ የደህንነት ሹሙ ጌታቸው አሰፋ የህወሃት ስራ አስፈጻሚ ሆኖ ተመርጧል።
በሌላ በኩል የህወሃት አመራሮች በአባሎችና ደጋፊዎቹ ቁጣና ተግሳጽ ደርሶባቸዋል። በስብሰባው ላይ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች በሙስናና ብልሹ አሰራር መዘፈቃቸውን ፣ህዝብ የሞተለትን አላማ በመርሳት ከደርግ ባልተናነሰ አምባገነነን መሆን ደረጃ መደረሱን ተራ አባላት በግልጽ ተናግረዋል።
የመቀሌው ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው የጉባኤው ተሳታፊዎች እንዳረጋገጡት የህወሃት ከፍተኛ አመራሮች የታገሉለትን አላማ በመርሳት በህዝብ ላይ እየፈነጬ መሆናቸውን ፣እነዚህ ሰዎች ከአድራጎታቸው እንዲታቀቡ አስጠንቅቀዋቸዋል። አብዛኛውን ማስጠንቀቂያ ሰጡት ደግሞ የህወሃት የገበሬ አባሎች ናቸው።
ይህ የህወሃት ገበሬዎች ቁጣ በመቀሌ ከተማ ከተሰማ በሃላ ነዋሪዎች ድጋፋቸውን በግልጽ ማንጸባረቃቸው የህወሃት ሙሰኛ አመራሮችን ጀምበር እያዘቀዘቀ መሆኑ ምልክት ተደርጎ ተወስዶአል።
በተለይ በዚህ መሰል ጉባኤ ላይ ጠንካራና መራር ተቃውሞ በህወሃት አባላትና ካድሬዎች ሲቀርብ ይህ የመጀመሪያ መሆኑን ያስረዱት ተሳታፊዎች ፣ ይህ ጅምር ራሱን ከህግ በላይ አድርጎ ለሚንቀሳቀሰው ቡድን ጥሩ ምልክት አይደለም በማለት መናገራቸውን ዘጋቢያችን ገልጿል።
ነገ የሚጀመረውን የኢህአዴግ ጉባኤ ተከትሎ መቀሌ በከፍተኛ ጥበቃ ስር ወድቃለች። የጸጥታውን ስራ የክልሉን ፖሊስ በመተካት የታጠቁ የፈዴራል ፖሊሶች በፖትሮል የታገዘ ጥበቃ እያከናወኑ ነው።