ኢሳት (ግንቦት 4 ፥ 2008)
የህወሃት ታይ በነበሩት በእነ ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የሚመራው የመሰረታዊ ብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክ ከውጭ ሃገር በሚገቡ የመለዋወጫ ዕቃዎችን በሞኖፖል እንዲያዝ በመደረጉ በመንግስት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያስከተለ መምጣቱ ተገለጸ።
መለዋወጫዎቹን ቶሎ ባለማቅረቡም ፋብሪካዎች ተበላሽተው ያለስራ ብዙ ጊዜያት ለመቆየት እንደሚገደዱ፣ ዕቃው ሲገኝም በውድ ዋጋ እንደሚቀርብላቸው ተመልክቷል።
ይህንን ያጋለጡት የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የስራ ሃላፊዎች መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ የስኳር ኮርፖሬሽን የስራ ሃላፊዎች በሳምንቱ መጀመሪያ በፓርላማው የመንግስት ልማት ድርጅት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፊት ቀርበው በሰጡት ምስክርነት ለኮርፖሬሽኑ መዳከም በምክንያትነት የሚጠቀሰው መሰረታዊ ብረታ ብረት ኮርፖሬሽን፣ ለቀድሞዎቹ የስኳር ፋብሪካዎች ጭምር መለዋወጫ እንዲያቀርብ ሃላፊው ስለተሰጠው፣ ለኮርፖሬሽኑ ተጨማሪ ችግር ሆኖ መገኘቱን አመልክቷል።
በ2003 በታወጀው የአምስት አመት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ በአምስት አመታት ይገነባሉ የተባሉትን 10 የስኳር ኮርፖሬሽኖች ለመገንባት ሃላፊነት የወሰደው የመሰረታዊ ብረታ ብረት ኮርፖሬሽን አንዱን እንኳን ካለመጠናቀቁም ባሻገር ለነባሮቹንም ጭምር መለዋወጫ እንዲያቀርብ ተወስኖለታል። በዚህም መሰረት ከኮርፖሬሽኑ ላይ ከፍተኛ ትርፍ እየሰበሰበና የቀደሙትንም እያደከመ መሆኑን የኮሮፖሬሽኑ ሃላፊዎችን ግንቦት 1 ቀን 2008 ለፓርላማው የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ገልጸዋል። ሜቴክ በወቅቱ መለዋወጫ ስለማቅረብ ነባሮችም ፋብሪካዎች ያለምርት ለቀናት ለመቆየቱ ይገልጻሉ።
“የማይችሉትን ሁሉ እንችላለን እያሉ አገርን ዋጋ እያስከፈሉ ነው። ምክንያቱም ነባሮቹ ፋብሪካዎች ያለችግር ቢሰሩ ቢያንስ በውጭ ምንዛሪ ስኳር አናስገባም ነበር” በማለት የኮርፖሬሽኑ ሃላፊዎች ለፓርላማው አባላቱ በቁጭት መናገራቸውን ከሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባ መረዳት ተችሏል።
የስኳር ኮርፖሬሽኑ ሃላፊዎች በህወሃት የቀድሞ ታጋዮች የተያዘው የመሰረታዊ ብረታ ብረት ኮርፖሬሽን ሚቴክ እንዴት ኮርፖሬሽኑን እንደሚበዘብዙም ሲገልጹ፣ “ለምሳሌ አንድ የስኳር ፋብሪካ ማብለያ ማሽን (ሮለር) ከውጭ ስንገዛ ከ200 ሺህ ብር አይበልጥም ፣ ሜቴክ ግን 600 ሺህ ነው የሚሸጥልን” በማለት ከአንድ ዕቃ ላይ የ2 መቶ ፐርሰንት ጭማሪ ወይም 400ሺ ብር ተጨማሪ ክፍያ እንደሚቀርብላቸው አረጋግጠዋል።
ሚቴክና በስኳር ኮሮፖሬሽኑ ያለው ግንኙነት በቢዝነስ ህግ የማይመራ በወጥ፣ በህግና በስርዓት ያልታሰረ መሆኑን የገለጹት ሃላፊዎች፣ ”እንቢ ብለን እንኳን እንዳንታገል አመራሮቹ ያሸማቅቁናል” በማለት መናገራቸውን ሪፖርተር ዘግቧል። የሚቴክ ሃላፊው የህወሃቱ የቀድሞ ታጋይ ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ሲሆኑ፣ የስኳር ኮርፖሬሽኑን ለረጅም አመታት በዳይሬክተርነት የመሩትና በሂደቶቹ ላይ ሁሉ መሪ ተዋናይ ሆነው የዘለቁት የህወሃቱ መስራችና አንጋፋ ታጋይ አቶ አባይ ጸሃዬ ናቸው። ለስኳር ኮርፖሬሽኑ መውደቅ ትልቁ ድርጃ የመሰረታዊ ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ነው ያሉት የስኳር ኮርፖሬሽን ሃላፊዎች የቀድሞዎቹ የስኳር ኮርፖሬሽኑ አመራሮች መጠየቅ አለባቸው በማለትም እነ አቶ አባይ ፀሃዬን ተጠያቂ አድርገዋል።