ጥር ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ክልል ዋና ከተማ ሃዋሳ በተለምዶ አረብ ሰፈር አሮጌ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ የበረንዳ ዳሶችን ካንድ ቀን በፊት ብቻ ማሰጠንቀቂያ በመስጠት አፍራሽ ግብረ ኃይል በማሰማራት ሕገወጥ ግንባታ በሚል ሱቆቹን ማፍረሱ ቀጥሏል።
ሕጋዊ የቫትና ቲኦቲ ግብር ከፋይ የሆኑት ነጋዴዎች ሁኔታውን በመቃወም ተቃውሟቸውን ቢገልፁም፣በአፀፋው የክልሉ ፖሊስ ሰላማዊ ሰልፈኞቹን በመደብደብ አካላዊ ጉዳት ከመፈፀሙ በተጨማሪ የተቃውሞው መሪ ያሉዋቸውን ነጋዴዎች ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስደው ስማቸውን መዝግበው ለቀዋቸዋል።
የከተማውን ውበት ያበላሻል በሚል አጥጋቢ ባልሆነ ምክንያት ቀድሞ ተፈቅዶላቸው የሰሩዋቸው የንግድ ቦታዎች የፈረሱባቸው ከ200 በላይ የሚሆኑ ነጋዴዎች ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ተጋጭተዋል። የአካባቢው ነዋሪዎችም ድጋፋቸውን ለነጋዴዎች ሰጥተዋል።
ነጋዴዎቹ በብረትና በጣውላ የከለሉዋቸውን ቦታዎች በአፍራሽ ግብረ ኃይሉ በመፍረሱ እቃዎቻቸው በዝናብና በፀሃይ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በዚህም ምክንያት እጅግ የከፋ ኪሳራና ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል።
በሃዋሳ ከተማ በቅርቡ በሬክተር ስኬል መለኪያ 4.5 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ መድረሱ ይታወቃል። በተለይ በከተማዋ ውስጥ ባሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ የመሬት መንቅጠቀጡ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፣ በሃዋሳ ዩንቨርሲቲ ዋናው ግቢና ሪፈራል ግቢ ውስጥ ብዙ ተማሪዎች ተጎድተዋል።
በንብረት ውድመት በኩልም የትምህርት ቤቶቹ ሕንጻ ግድግዳዎች ተሰነጣጥቀው መስታወቶቻቸውም ረግፈዋል። ዛሬ ተማሪዎቹ ለ15 ቀናት ትምህርታቸውን አቋረጠው ከግቢው ወጥተው ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ የዩንቨርሲቲው አስተዳደር ማስታወቂያ በመለጠፍ ትምህርት መቋረጡን ገልጿል።