በሃዋሳ ከተማ የጨምበለላን በዓል ተከትሎ ግጭት ተነሳ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 5 ቀን 2010 ዓ/ም) በተለያዩ ደማቅ ዝግጅቶች የሚከበረው የሲዳማ ማህበረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል ፣ ጨምበለላ፣ በአዋሳ ከተማ በሚከበርበት ወቅት ያልታሰበ ግጭት ተነስቷል። በግጭቱ የተገደሉ ሰዎች መኖራቸውን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ከተማዋ በታጠቁ ሀይሎች ተሞልታለች። ሲዳማ ወጣቶች በባህላዊ ዜማ በቡድን በቡድን ሆነው እየዘመሩ ተቃውሞአቸውን ቢያሰሙም፣ ባለ ቀይ መለዮ ወታደሮች በዱላ እና በሰደፍ እየደበደቡ ለመበተን ሲጥሩ መታየታቸውን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ግጭቱ ሆን ተብሎ በደኢህዴን ባለስልጣናት እንደተነሳ፣ በተለይም የአዲሱን ጠ/ሚኒስትር ወደ ስልጣን መምጣት ያልተቀበለው የደኢህዴን ቡድን ፣ የዶ/ር አብይን ምስል የያዘ ቲሸርት እንዳይለበስ በመከልከላቸው ውዝግብ መፈጠሩን ይናገራሉ። የሲዳማ ተወላጆች ሃዋሳ በክልል ደረጃ እንዲዋቀር ጠ/ሚኒስትሩ ከተማዋን በጎበኙበት ወቅት መጠየቃቸውን፣ ይህንኑ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ሲጠየቁ መዋላቸውን ነገር ግን የክልሉ ባለስልጣናት ግጭት እንዲፈጠር ሆን ብለው የተደራጁ ቡድኖችን መላካቸውን ስፍራው ላይ የነበሩና ድርጊቱን ሲከታተሉ የነበሩ ለኢሳት ገልጸዋል።
በጉዳዩ ላይ የደኢህዴን ባለስልጣናት የሰጡት መግለጫ የለም። ጨምበለላ የሲዳማ ተወላጆች ባህላዊ ልብሶችን ለብሰው፣ አዛውንቱ መልካም ምኞታቸውን በምርቃት እየገለጹ፣ ወጣቶች እየጨፈሩ የሚያከብሩት ባህል ነው።
ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የሃገር ሽማግሌዎች “የቄጣላ” ጨዋታ፣ የፈረስ ጉግስን ጨምሮ የተለያዩ ዝግጅቶችን ያከናውናሉ።
ይህ አለማቀፍ እውቅና ያገኘው በዓል፣ ለሚቀጥሉት 2 ሳምንታት ይከበራል።