በሃረር እና ደሴ ከተሞች ከሚፈርሱ ቤቶች ጋር በተያያዘ በርካታ ቤተሰቦች ለችግር ተዳርገዋል

ግንቦት ፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አቶ በላይነህ ተስፋዬ የተባሉ የሃረሪ ክልል ምክር ቤት አባል እና ባለሃብት፣ ህዳር 29፣ 2009 ዓም ለሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች በአል በአምስት ወራት ውስጥ 75 ሆቴሎችን እገነባለሁ በሚል ከ30 በላይ መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ድርጅቶችን እንደፈርሱ በማስደረጋቸው ከ300 ያላነሱ ዜጎች ችግር ላይ መውደቃቸውን ወኪላችን ከስፍራው ዘግቧል። የአንዳንድ ነጋዴዎች የንግድ ድርጅቶች ከ 30 እና 40 አመታትን ያስቆጠሩ ሲሆን፣ ነጋዴዎቹ ነባር ይዞታቸውን ለማልማት ቦታቸውን በሊዝ ገዝተው ግንባታ ለመጀመር እንቅስቃሴ ላይ ነበሩ።
ቤታቸው የፈረሰባቸው ሰዎች እቃዎቻቸውን እንኳ ማንሳት ተከልክለው ንብረታቸውን መዘጋጃ መውሰዱን ወኪላችን ገልጿል።
በተመሳሳይ ዜና ጀጎልን ለማልማት በሚል ያለፍላጎታቸው እንዲነሱና በአቡበክር ወረዳ ውስጥ በተሰራው ኮንዶሚኒየም እንዲኖሩ የተደረጉት ነዋሪዎች በመብራትና ውሃ እጦት ሲሰቃዩ ከቆዩ በሁዋላ፣ አሁን ደግሞ ለቤት ኪራይ በየወሩ 400 ብር እንዲከፍሉ መጠየቃቸው ጭንቀትን እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። ቀድሞ ይኖሩበት በነበረው የቀበሌ ቤት ውስጥ ከ4 ብር እስከ 8 ብር ይከፍሉ እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ አሁን በድንገት በየወሩ 400 ብር እንዲከፍሉ መታዘዛቸው እንዳስደነገጣቸው ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ ክፍያውን እንዲጀምሩ ፣ ክፍያውን መፈጸም የማይችሉ ከሆነ ደግሞ ቤቶቹን ለቀው እንደሚወጡ ተነግሯቸዋል። አብዛኞቹ እንጀራ በመሸጥ የሚተዳደሩ ፣ የጉልበት ስራ ሰርተው የሚኖሩና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የመንግስት ሰራተኞች ሲሆኑ፣ ብዙዎቹ ነዋሪዎች የአማራ እና የጉራጌ ብሄረሰብ ተወላጆች ናቸው። ነዋሪዎቹ የክልሉ መንግስት በብሄራችን የተነሳ አድልዎ እየፈጸመብን ነው በማለት ቅሬታቸውን ያሰማሉ።
በዚሁ ክልል በአሚር ወረዳ ልዩ ስሙ ገንደቦኤ በሚባል አካባቢ በህገወጥ መንገድ ተገንብተዋል የተባሉ መኖሪያ ቤቶች ከፈረሱ በሁዋላ፣ “የኦሮሞን ቤቶች ለይታችሁ ያፈረሳችሁ የሃረሪ ባለስልጣናት ኦነግ በቅርቡ እርምጃ እንደሚወስድባችሁ ያስታውቃል” የሚል በኦሮምኛና በአማርኛ የተጻፉ በራሪ ወረቀቶች መበተናቸውን ተከትሎ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ መግባታቸውንና ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን ወኪላችን አክሎ ገልጿል። የመንግስት መስሪያ ቤቶች በልዩ ሁኔታ እየተጠበቁ ቢሆንም፣ ይህን ዜና እሳከጠናከርንበት ሰአት ድረስ የተፈጠረ ነገር አለመኖሩ ታውቋል።
በደሴ ከተማ ደግሞ መድሃኒአለም አካባቢ የሚኖሩ በነአስተኛ የንግድ ስራዎች ላይ ተሰማርተው የሚኖሩ ነዋሪዎች አካባቢውን እንዲለቁ ታዘዋል። ከግንቦት8፣ 2008 ዓም ጀምሮ የመንግስት አፍራሽ ግብረሃይሎች ቤቶችን ማፍረስ የጀመሩ ሲሆን፣ አንዳንድ ነዋሪዎች ቤቶቻችንን አናስፈርስም በማለት ተቃውሞ እያሰሙ ነው።