በሃረር ታስረው ከሚገኙት መካከል የ3ቱ የዋስትና መብት ተከበረ

ሰኔ ፳(ሃያ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከወራት በፊት በሃረር ከተማ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ተከትሎ ከታሰሩት ነጋዴዎች መካከል የዋስትና መብት ተከልክለው የነበሩት በቢንያም መንገሻ መዝገብ የተከሰሱት 3ቱ ነጋዴዎች በ20 ሺ ብር ዋስትና እንዲፈቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰጥቷል። ነጋዴዎቹ ያወስትና መብት መከልከላችን ትክክል አይደለም በሚል ይግባኝ ብለው ነበር።

በሌላ መዝገብ የተከሰሱት 21 ተከሳሾች ደግሞ ዳኛ አልተሟላም በሚል ለፊታችን ሃሙስ ሰኔ 25 ቀን 2006 ዓም ተቀጥረዋል።

እስካሁን ድረስ ክስ ያልተመሰረተባቸው 3 የመብራት ሃይል ሰራተኞች እና 3 ነጋዴዎች ያለፉትን 4 ወራት በእስር ማሳለፋቸው ታውቋል። ፖሊሶች ሆን ብለው ሰዎችን እያሰቃዩዋቸው መሆኑን የሚገልጸው ወኪላችን አንደኛው እስረኛ የአካል ጉዳተኛና የ4 ልጆች አባት በመሆኑ ቤተሰቡ በሙሉ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጧል ብሎአል። አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ጠበቃ ” በህይወቴ እንዲህ አይነት የሰብአዊ መብት ጥሰት አይቼ አለውቅም” በማለት እስረኞች ስለሚደርስባቸው ግፍ ተናግረዋል።

በሸዋ በር ገበያ የደረሰውን ቃጠሎ የክልሉ መስተዳድር እንደፈጸመው አብዛኛው የከተማው ህዝብ እንደሚያምን ወኪላችን አክሎ ገልጿል።