በሃረር ለሚደረገው የብሄረሰቦች በአል 500 ሚሊዮን ብር በጀት ተያዘ

ሚያዚያ ፲፪(አሥራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የክልሉ ምንጮች እንደገለጹት ህዳር 29 ለሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ግማሽ ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን፣ ገንዘቡም ከሃረረ ስታዲየም እስከ አመሬሳ የሚደረሰውን 3.3 ኪሜ ባለሁለት መስመር መገድ ለማሰራት እንዲሁም፣ ከውጭ ለሚመጡ ዲያስፖራ እንግዶች ማረፊያ 600 ባለ አንድ ፎቅ ቤቶችን ለመገንባት እና ከተማዋን ለማጽዳት ይውላል ተብሎአል።
ለመንገድና ለቤቶች መስሪያ በሚል በሃኪም ወረዳ የሚገኙ 250 ነዋሪዎችና የንግድ ድርጅቶች ከቦታቸው እንዲነሱ የተደረገ ሲሆን፣ ዜጎቹ እስካሁን ተገቢውን ካሳ ባለማግኘታቸው አቤቱታ እያሰሙ ነው።
በብሄር ብሄረሰቦች ቀን ሰበብ ከፍተኛ ሙስና እንደሚፈጸም ኢሳት በተደጋጋሚ ሲዘግብ መቆየቱ ይታወቃል።