በሃረሪ ክልል ፕሬዚዳንቱን ከተቹት ውስጥ አብዛኞቹ ተፈቱ
ግንቦት ፳፱(ሃያ ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የክልሉን ፕሬዚዳንትና ሌሎችም ባለስልጣናት በሙስ እና በመልካም አስተዳደር እጦት በመተቸት፣ ፓርቲውን እና ክልሉን ሊያፈርሱ ተነስተዋል በሚል በሽብርተኝነት ወንጀል ከተከሰሱት 6 ወጣቶች መካከል 4ቱ ከቀጠሮው በፊት ባለፈው ሳምንት ፖሊስ አስቀድሞ ሲፈታቸው፣ ሁለቱ ደግሞ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው አንደኛው በ5 ሺ ባር ዋስ እንዲወጣ ሲደረግ ሌላኛው ተከሳሽ መርዋን የሱፍ ተጨማሪ የ10 ቀናት ጊዜ ተጠይቆበታል። በችሎቱ በርካታ ታዳሚዎች የተገኙ ሲሆን፣ ፖሊስ ተጨማሪ ቀጠሮ በመጠየቁ ህዝቡ ተቃውሞ ሲያሰማ ታይቷል። ሰዎቹ እንዲፈቱ የክልሉ ህዝብ ከፍተኛ ግፊት ማድረጉንና አስተዳደሩን ስጋት ላይ መጣሉን ወኪላችን ገልጿል።
በሌላ በኩል ከቤት ቃጠሎና ከይዞታ መፈናቀል ጋር በተያያዘ የታሰሩ ከ50 በላይ ዜጎች ሽብርተኞች ተብለው እስከዛሬ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከአመት በላይ ታስረው ይገኛሉ። እስር ቤት ውስጥ የሚገኙት ሁሉም የሌሎች ብሄረሰቦች ተወላጆች ናቸው።
ባለፈው ቅዳሜና እሁድ የሸንኮር ወረዳ ባለስልጣናት በወጣቶች ማእከል አዳራሽ ውስጥ የጠሩትን የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ ስብሰባ ህዝቡ አንሳተፍም ብሎ የቀረ ሲሆን፣ በስብሰባው ላይ የተገኙት የኦህዴድና የሃብሊ አባላት እርስ በርስ በመዘላለፍ ስብሰባው ተጠናቋል። የሃረሪ ብሄራዊ ሊግ ደጋፊዎች ፣ እናንተ መረጃዎችን ለኢሳት እየሰጣችሁ ትዘግባላችሁ በማለት መሳደቡዋን ተከትሎ ሌሎች የኢህአዴግ ደጋፊዎች ቁጣቸውን አሰምተዋል። በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች፣ ዳኞችና ጠበቆች ግለሰቧ ለፍርድ እንድትቀርብ ካልቀረበች ስራ አንሰራም ብለው ሲታመሱ ውለዋል።
ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር የተደረገውም ስብሰባ እንዲሁ ተሰብሳቢዎች “ ጊዜያችንን ለምን ታቃጥሉብናላችሁ፣ እናንተ የሌሎችን ብሄረሰቦች ጉዳይ አታዩም” የሚሉና ሌሎች ትችቶችን በማቅረብ ተቃውሞዋቸውን ማሰማቱን ወኪላችን ገልጿል።
2016-06-06